የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር 6ኛ የስራ ዘመን 13ኛ ጉባኤው በሁለት ቀናት ውሎው በልዩ ልዩ አጃዳዎች ላይ መክሮ ውሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ለክልሉ ህብረተሰብ ልማትና መልካም አስተዳር ፋይዳ ያላቸውን ሶስት አዋጆችንና አንድ ደንብ አጽድቋል፡፡
በምክር ቤቱ ቀርበው ሰፊ ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ የጸደቁ አዋጆችም የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ቅርሶችን ለመጠበቅ የወጣ ረቂቂ አዋጅ፣ የክልሉ ፍርድ ቤት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ፣ የዋናው ኦዲት መስሪያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅን እንደገና ለማሻሻል የወጣ ረቂቅ አዋጅ እና የዋና ኦዲት መስሪያ ቤት የሠራተኞች አስተዳደር ረቂቅ ደንብ ናቸው፡፡
በማስከተልም የዕጩ ዳኞች ሹመት በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት በክቡር አቶ ሙሉጌታ አጎ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ጸድቋል፡፡
ዳኝነታቸው የጸደቀላቸው ዕጩ በከበረው ምክር ቤት ቀርበው ቃለ መሃላ የፈጸሙ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት 22 ዳኞች፣ ለወረዳ እና ከተማ አስተዳደር መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች 124 ዳኞች በአጠቃላይ 146 ዳኞችን ሹመት በማጽደቅ ጉባኤው መጠናቀቁን ከምክርቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
