የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች WT Media በክልሉ ላይ እየፈጠረ ያለው ተጨባጭ ተፅዕኖ እያሳሰባቸው መሆኑንና ይህንን ተፅዕኖ ለመቀነስም ለቢሮ ኃላፊዎችና ለሠራተኞች ጥብቅ መመሪያ በዛሬው ዕለት መስጠታቸው ተጋልጧል።
ከየቦታው ለዝግጅት ክፍላችን የደረሱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ለሁሉም የማዕከል ቢሮ ኃላፊዎች የሚሆን አጭር የጽሑፍ ሰነድ አዘጋጅተው አሰራጭተዋል።
ምንም እንኳ ሰነዱ በመድረኩ ለሠራተኞች በቀጥታ ባይታደልም፣ በየመሥሪያ ቤቱ በተደረጉ ስብሰባዎች ላይ በቃል ብቻ እንዲቀርብ ተደርጓል።
በስብሰባው ላይ የቀረበው ዋና አጀንዳ “WT Media በክልሉ አጀንዳ እየቀረጸ ነው፤ በክልሉ የመንግሥትና የማኅበራዊ ሚዲያዎቻችን በዚህ ሚዲያ ተበልጠዋል” የሚል ሲሆን፣ መንግሥት ከፍተኛ በጀትና ሎጀስቲክ እየመደበ ባለበት ሁኔታ በአጀንዳ ቀራጭነት (Agenda Setting) እንዴት ሊሸነፍ እንደቻለ ጥያቄ ቀርቧል።
በውይይቱ ወቅት ሠራተኞች በሰጡት አስተያየት፣ ሰሞኑን የቀድሞው ከፍተኛ የክልሉ ባለሥልጣን አቶ ዳዊት ገበየሁ ለ WT Media የሰጡት መረጃዎች አብዛኞቹ እውነተኛና ተጨባጭ በመሆናቸው መንግሥት በጉዳዩ ላይ ግልጽ ማብራሪያ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።
በሌላ በኩል፣ “የመንግሥት ሚዲያ ድክመት በሠራተኛው ላይ ሊደፈደፍ አይገባም፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ብቻ ይወያዩበት” በሚል አንዳንድ ሠራተኞች ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው ታውቋል።
ከሁሉ በላይ አሳሳቢው መረጃ የወጣው ባለፈው ሳምንት ከተካሄደው የክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት ስብሰባ ነው።
በስብሰባው ላይ “WT Media ከውጭ አገር ሆኖ ሥራችንን በአግባቡ እንዳንሠራ እያደረገን ስለሆነ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ወደ ኢትዮጵያ አምጥቶ ማሰር ወይም ባለበት አገር ላይ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል” የሚል አቋም ተይዟል።
ይህንን ተልዕኮ ለማስፈጸምም አንድ ልዩ የአስፈጻሚ ኮሚቴ መዋቀሩን ከስብሰባው ተሳታፊዎች መካከል አንዱ ለ WT Media አረጋግጧል።
WT Media የሕዝብ ድምፅና የጭቁኖች ተሟጋች ሆኖ ሥራውን ይቀጥላል። መንግሥት በሐሳብ ከመሞገትና በደልን ከማረም ይልቅ፣ እውነትን የሚያወጡ የሚዲያ ባለሙያዎችን ለማሳደድና ለማሰር የሚያደርገው ጥረት የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ይበልጥ የሚያቆረቁዝ መሆኑን እናሳስባለን። የትኛውም ዓይነት ማስፈራሪያ ከጀመርነው የእውነት መንገድ አያናውጠንም።