1000105095

ለ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ከአንድ ጊዜ በላይ የመራጭነት ካርድ ሲወስዱ መታየታቸው በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ጥርጣሬና ጥያቄ እየቀሰቀሰ ይገኛል።

WT Media ያደረጓቸው ማጣራት፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አለምነሽ ደመቀ ባለፈው ሳምንት በአንድ የምርጫ ጣቢያ ተገኝተው የመራጭነት ካርድ ለመውሰድ ተሰልፈው ወስደው ነበር።

ይሁን እንጂ በዛሬው ዕለት በጋሞ ዞን ገረሰ ምርጫ ክልል በድጋሚ ተገኝተው ሌላ የመራጭነት ካርድ ሲወስዱ መታየታቸውን መረጃዎች አረጋግጠዋል።

ይህንን ሁኔታ የታዘቡ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎችና የታዘቢዎች የሚከተሉትን ጥያቄዎች እያነሱ ይገኛሉ።

ለክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከአንድ ጊዜ በላይ በተለያዩ ጣቢያዎች የመራጭነት ካርድ እንዲወስዱ የተፈቀደ ልዩ ሕግ አለ ወይ?

ይህ ተግባር የምርጫውን ተዓማኒነትና የ ‘አንድ ሰው አንድ ድምፅ’ መመሪያን የሚጥስ አይደለም ወይ?

በክልሉ ሌሎች ባለሥልጣናትስ ተመሳሳይ ድርጊት እየፈጸሙ ይሆን?

እንደ ኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ፣ ማንኛውም ዜጋ የመራጭነት ካርድ መውሰድ የሚችለው በአንድ የመኖሪያ አካባቢና በአንድ የምርጫ ጣቢያ ብቻ ነው።

ከአንድ በላይ ካርድ መያዝ ወይም በተለያዩ ቦታዎች መመዝገብ በሕግ የሚያስጠይቅ የምርጫ ሥነ-ምግባር ጥሰት ነው።

የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለሕግ የበላይነት ምሳሌ መሆን ሲገባቸው፣ እንዲህ ዓይነት አጠራጣሪ ድርጊቶች ውስጥ መገኘታቸው ምርጫው ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ እንዳይሆን እንቅፋት ሊፈጥር ይችላል የሚል ሥጋት በሰፊው እየተንጸባረቀ ነው።

WT Media ጉዳዩን በሚመለከት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ከሚመለከታቸው አካላት ማብራሪያ ለማግኘት ጥረት እያደረገ ሲሆን፣ ተጨማሪ መረጃዎችን እንደደረሱን ለሕዝብ ይፋ እንደምናደርግ እንገልጻለን።