GridArt_20260327_211915947

በሐዋሳ ከተማ ሐይቅ ዳር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩ ከ200 በላይ አባወራዎች፣ ምንም ዓይነት አማራጭ ሳይሰጣቸውና የቅድመ ዝግጅት ጊዜ ሳይሰጣቸው በከተማ አስተዳደሩ “በአንድ ሳምንት ውስጥ ቤታችሁን ለቃችሁ ውጡ” መባላቸውን ገልጸው ለ WT Media አሳዛኝ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

ነዋሪዎቹ ለሚዲያችን በላኩት የሰነድ፣ የድምፅና የቪዲዮ መረጃ መሠረት፣ የአካባቢው አስተዳደር ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ምትክ ቦታ በሰባት ቀናት ውስጥ እንዲለቁ ትዕዛዝ አስተላልፎባቸዋል።

ነዋሪዎቹ “ንብረታችንን ጥለን ወደየት እንሄዳለን?” በማለት ከፍተኛ ጭንቀትና እንግልት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ በአካባቢው ከ50 ዓመታት በላይ የኖሩና ንብረት ያፈሩ መሆናቸውን በምሬት ይናገራሉ።

በቪዲዮ ምስክርነታቸው ላይ አንዲት እናት በለቅሶ የታጀበ ድምፅ ሲናገሩ፦ “ለ50 ዓመት የኖርንበትን ቤት በ7 ቀን ውስጥ ውጡ ተብለናል፤ ልጆቻችንንና ንብረታችንን ይዘን የት እንውደቅ?” በማለት የደረሰባቸውን ግፍ ይገልጻሉ።

WT Media ከነዋሪዎቹ የደረሱትን መረጃዎች መርምሯል። በዚህም የነዋሪዎቹን መኖሪያ ቤቶችና አካባቢውን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች የደረሱን ሲሆን፣ ቤቶቹ ለረጅም ጊዜ የቆዩ መሆናቸውን ያመለክታሉ።

የነዋሪዎችን የጋራ ጩኸትና የደረሰባቸውን እንግልት በዝርዝር የሚያስረዳ የድምፅ፣ የሰነድና የቪዲዮ ፋይል ለዝግጅት ክፍላችን ደርሷል (ለቅሬታ አቅራቢዎች ደህነነት ሲባል አላቀረብንም)።

ነዋሪዎቹ ፕቲሽን በመፈራረም በሰፈር መሪዎቻቸው አማካኝነት በይፋ ቅሬታ ለከተማ አስተዳደሩ ያስገቡ ቢሆንም እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውንም ገልጸዋል።

አምስት አስርት ዓመታትን ያስቆጠረ ይዞታን ያለምንም ምትክና በቂ የዝግጅት ጊዜ እንዲለቀቅ ማዘዝ ሰብዓዊነት የጎደለውና ሕገ-መንግሥታዊ መብትን የሚጥስ ተግባር መሆኑን የሕግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡ ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው ያልተሳካ ቢሆንም ምላሽ ከተገኘ የአስተዳደሩን ምላሽ እናቀርባለን።

የነዋሪዎቹ ጩኸትና እንግልት የሚመለከተው የመንግሥት አካል ዘንድ ደርሶ አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ WT Media ጉዳዩን መከታተሉን ይቀጥላል።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media

1 thought on “በሐዋሳ ከተማ የ50 ዓመት ቤታቸው በአንድ ሳምንት እንዲፈርስና እንዲለቁ የታዘዙ የ200 አባወራዎች አሳዛኝ ቅሬታ አቀረቡ”

Comments are closed.