የአካል ጉዳተኝነት ለዓላማ ጽናት እንቅፋት ሊሆን እንደማይችል በተግባር ያሳየውና በኤሌክትሪክ አደጋ ሁለት እጆቹን ያጣው ወጣት፣ ዛሬ ግን ከጉዳቱ በላይ የሥራ ዕድል መከልከልና የመንግሥት ቸልተኝነት ክፉኛ እየጎዳው መሆኑን በምሬት ገልጿል።
ወጣቱ በ2000 ዓ.ም ትምህርቱን አቋርጦ በሐዋሳ ከተማ በሥራ ላይ እያለ በደረሰበት የኤሌክትሪክ አደጋ ሕይወቱ በተአምር ቢተርፍም፣ ሁለት እጆቹን ግን ሙሉ በሙሉ አጥቷል።
ይሁን እንጂ ይህ ከባድ ፈተና ከዓላማው አላገደውም። በከፍተኛ ጥንካሬ ትምህርቱን በመቀጠል ወደ ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ በመግባት፣ ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት በኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪውን ማግኘት ችሏል።
ኢንጂነር ሆኖ ተመርቆ የወጣው ይህ ብርቱ ወጣት፣ ላለፉት ስድስት ዓመታት በየመሥሪያ ቤቱ ደጅ ቢጠናም በአካል ጉዳተኝነቱ ምክንያት ብቻ የሥራ ዕድል ተነፍጎታል።
“አካል ጉዳተኝነቴ ትምህርቴን እንዳልማር አላገደኝም፤ ዛሬ ግን ሥራ እንዳላገኝ እንቅፋት ሆኖብኛል” ሲል በቪዲዮው ላይ በቁጭት ይናገራል። የዚህ ወጣት ታሪክ በዎላይታ ዞን ያለውን ሰፊ ማኅበራዊ ቀውስ ማሳያ ነው።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዞኑ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው ሥራ ያጡ ወጣቶች ቁጥር ከ 200 ሺህ በላይ ደርሷል።
በአካባቢው የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ሌሎች ሰፋ ያሉ የሥራ ዕድል ፈጣሪ አማራጮች ባለመኖራቸው፣ ወጣቱ ትውልድ በከፍተኛ ድህነትና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ይገኛል።
መንግሥት ለዚህ ሰፊ የሰው ኃይል የሥራ ዕድል ከመፍጠር ይልቅ ቸልታን መምረጡ ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል። WT Media የዚህን ጀግና ወጣት በቋሚነት የሚደገፍበትንና የሥራ ዕድል የሚያገኝበትን መንገድ ለማመቻቸት ይፈልጋል።
በተጨማሪም መንግሥት በዎላይታ ዞን ያለውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ትኩረት እንዲሰጥና ለነዚህ አምራች ወጣቶች አማራጭ የሥራ መስኮችን እንዲያመቻች እናሳስባለን።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media