GridArt_20260402_152550623

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በዎላይታ ሶዶ ከተማ የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾችን በመቅደድ ለብስኩት መጠቅለያነት ሲጠቀም የተገኘ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የከተማው ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

ድርጊቱ በከተማው ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።

እንደ ፖሊስ መግለጫ ከሆነ፣ በትናንትናው ዕለት መጋቢት 23 ቀን 2018 ዓ.ም በአራዳ ክፍለ ከተማ፣ ሕብረት ቀበሌ ውስጥ አቶ ሽኩር መሐመድ የተባለና በሻይ ቤት ንግድ የሚተዳደር ግለሰብ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመቅደድ ለንግድ አገልግሎት ሲጠቀም ተገኝቷል።

ፖሊስ ከሕዝብ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ግለሰቡን ወዲያውኑ በቁጥጥር ሥር አውሏል።

ፖሊስ በመግለጫው ያሰፈራቸው ዋና ዋና ነጥቦች ግለሰቡ ለዚህ ድርጊት ሕፃን ልጅ መጠቀሙ የተረጋገጠ ሲሆን፣ የንግድ ቤቱም እንዲታሸግ ተደርጓል።

በአሁኑ ወቅት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሠረት ተጨማሪ ምርመራና ፍተሻ እየተካሄደ ይገኛል።

ድርጊቱ በሃይማኖቶች መካከል ግጭት ለመፍጠርና የሶዶን ከተማ ሰላም ለማናጋት የታለመ ቢሆንም፣ የከተማው ሕዝብ ያሳየው ጨዋነትና ትዕግሥት የሚመሰገን መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።

ማኅበረሰቡ የፖሊስን የምርመራ ውጤት በትዕግሥት እንዲጠባበቅና ከጸጥታ አካላት ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።

የዎላይታ ሶዶ ከተማ ለዘመናት የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከባብረውና ተፋቅረው የሚኖሩባት የሰላም ተምሳሌት ናት።

እንዲህ ዓይነት ሃይማኖታዊ ስሜትን የሚነኩና ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚያረክሱ ድርጊቶች በማንኛውም ወገን ሊወገዙ የሚገባቸው ናቸው።

WT Media ጉዳዩን በትኩረት የሚከታተል ሲሆን፣ የፖሊስ የምርመራ ውጤትና ተያያዥ መረጃዎችን እንደደረሱን ለሕዝብ ይፋ እንደምናደርግ እንገልጻለን።