በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን በደረሰው አስከፊ የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የተሰበሰበው ወደ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለተጎጂዎች ሳይደርስ መመዝበሩንና ድርጊቱን ያስፈጸሙ አካላትም ከተጠያቂነት አምልጠው አዲስ ሹመት እየተሰጣቸው መሆኑን የ WT Media የምርመራ ዘገባ አመልክቷል።
ለጎፋ አደጋ ተጎጂዎች መልሶ ማቋቋሚያ ከተለያዩ ግለሰቦች፣ ረድኤት ድርጅቶችና ተቋማት የተሰበሰበውና ወደ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋው ገንዘብ የት እንደደረሰ እስካሁን በይፋ የታወቀ ነገር የለም።
WT Media ቀደም ብሎ በዘገባቸው መረጃዎች እንደጠቆመው፣ ይህ ከፍተኛ የሕዝብና የመንግሥት ገንዘብ ለተጎጂዎች ከመድረስ ይልቅ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና በግለሰቦች እጅ እንዲገባ ተደርጓል።
የቀድሞው የክልሉ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኃላፊ የነበሩት አቶ ጋንታ ጋምኣ፣ ይህንን ከፍተኛ የገንዘብ ማጭበርበር ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመመሳጠር በዋና አቀነባባሪነት ሲመሩ እንደነበር ይነገራል።
በቅርቡ በተደረገው ግምገማ በሙስና ቅሌቱ ምክንያት ከተጠያቂነት ለማስመለጥ ሲባል ብቻ ከነበሩበት ኃላፊነት እንዲነሱ ተደርጎ ነበር።
ይሁን እንጂ፣ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ መረጃው በሚዲያ ሳይሰማና የሕዝብ ትኩረት ሳይሳብ፣ ለግለሰቡ በምስጢር አዲስ ሹመት መስጠታቸው ለዝግጅት ክፍላችን አፈትልኮ የደረሰው መረጃ ያረጋግጣል።
አቶ ጋንታ ጋምኣ አሁን ላይ በክልሉ እጅግ ለሙስና ተጋላጭና ሰፊ በጀት በሚንቀሳቀስበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ግብዓት አቅርቦትና ስርጭት መሥሪያ ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል።
የመረጃ ምንጮቻችን እንደጠቆሙት፣ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ አቶ ጋንታን ወደዚህ ቁልፍ ቦታ የመለሷቸው በጎፋው የገንዘብ ምዝበራ ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ ራሳቸው እጃቸው ስላለበትና ተያይዞ የሚመጣን ተጠያቂነት ለመከላከል የተደረገ የጥቅም መለዋወጥ ሴራ ነው።
ሕዝቡ ጉዳዩን እየረሳ ነው በሚል ስሌት የተሰጠው ይህ ሹመት፣ በክልሉ ያለውን የሙስና መረብ ምን ያህል የተደራጀ መሆኑን ያሳያል።
እስከ ዛሬ ድረስ በጎፋ አደጋ ተጎጂዎች ስም የተሰበሰበው አንድ ቢሊዮን ብር የት እንደደረሰ ሳይታወቅና ወንጀለኞቹ በሕግ ሳይጠየቁ፣ እንዲህ ዓይነት የሹመት ሽልማት መሰጠቱ በክልሉ ሕዝብ ላይ የተፈጸመ ታሪካዊ ክህደት ነው።
WT Media የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን እንዲሁም የሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ምርመራ እንዲጀምሩና የተዘረፈው የደሃ ተጎጂዎች ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ይጠይቃል።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media