GridArt_20260403_140551970

ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ማለት በተለየ ሁኔታ ሕገ-መንግሥቱን በበላይነት የማስከበር ኃላፊነት በሕገ-መንግሥቱ የሚሰጠው የሕግ ተርጓሚ ፍርድ ቤት ነው።

ይህ ተቋም መኖሩ ለአንድ አገር የሕግ የበላይነትና ለዜጎች መብት መከበር ወሳኝ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግን አለመኖሩ ለብዙ መከራዎች በር ከፍቷል።

አርቆ አሳቢው ምሁር ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ በሽግግሩ ቻርተር ወቅት ያቀረበውና የሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ይቋቋም የሚለው ምክረ-ሐሳብ ተቀባይነት በማጣቱ፣ የዎላይታና መሰል ለመብታቸውና ለክብራቸው ቀናኢ የሆኑ ሕዝቦች ለተደጋጋሚ ስቃይ ተዳርገዋል።

ፕሮፌሰሩ በአንድ ወቅት ከሸገር ኤፍ ኤም (መአዛ ብሩ) ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ እንዲህ ብለው ነበር፦

< “ልዩ ልዩ የዴሞክራሲ መብቶች ቻርተሩ ላይ ወጥተዋል፤ አንዱ አብይ መብት ደግሞ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ነው። እነዚህ መብቶች እንደማንኛውም ዴሞክራቲክ መብት ሊጋጩ ይችላሉ።

ይህ በሚሆንበት ጊዜ የትኛው መብት ነው የበላይ የሚሆነው? የሚለው ጥያቄ አልተመለሰም። በሰብዓዊ መብቶች ላይ ከመንግሥት ቁጥጥር ነፃ የሆነ ችሎት ፍርድ ይሰጣል ቢባልም፣ ራስን በራስ የመወሰን ዕድል ላይ ግን ‘ችሎት አያገባውም’ ተባለ።”>

ይህ የሕግ ክፍተት ዛሬም ድረስ በሐገራችን ለሚታዩ ግጭቶችና የሥልጣን አለግባብ አጠቃቀሞች ዋነኛ መንስኤ ሆኖ ቀጥሏል።

የዎላይታ ሕዝብ ጥንታዊና የረቀቀ (advanced) የመንግሥት አስተዳደር የነበረው ታሪካዊ ሕዝብ ነው።

ከዱቡሻ እርቅ እስከ ሆሎዚ ስቅላት፣ ከዳና እስከ ካዎ አቤቱታ የሚቀርብበትና መልስ የሚገኝበትን ስልጣኔ ያዳበረ ሕዝብ ነው።

እነዚህ የባሕላዊ ዳኝነት፣ የፍትሕና የእርቅ ሥርዓቶች በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ሆነው እንዲመዘገቡ የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍልና የዞኑ አስተዳደር በትብብር ሊሠሩ ይገባል።

ይሁን እንጂ፣ ዎላይታ ወደ ኢትዮጵያ የተቀላቀለው ሰባት ዓመታትን በፈጀ ከባድ ጦርነት በመሆኑና የሃገርነት ትዝታ ያለው ሕዝብ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ጥላ ሥር ብዙ የተገፋበት አግባብ አለ። በኢሕአዴግ ዘመንም ቢሆን ዎላይታ ዞን የሆነው በከባድ መስዋዕትነት ነው።

በአሁኑ ወቅት ብልጽግና መራሹ መንግሥት የዎላይታ ሕዝብን የክልልነት ጥያቄ ለማፈን በሕገ-መንግሥቱና በመመሪያዎች ላይ “ጢባጢቤ” ተጫውቷል።

በዞኑ መፈንቅለ-መንግሥት ማካሄድ፣ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ለዓመት እንዳይሰበሰብ ማድረግ፣ ግልጽ ያልሆነ ሕዝበ-ውሳኔ ማካሄድና የሥልጣን መጋራት መብትን መንፈግ የሚጠቀሱ ጥሰቶች ናቸው።

የዎላይታ ሕዝብ አቤቱታ የሚያቀርብበት ገለልተኛ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ባለመኖሩ፣ ከወንድሞቹ ኢትዮጵያውያን ጋር ወደ ጦርነት ላለመግባት ሲል ብቻ ትልቅ ዋጋ እየከፈለ ይገኛል።

ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ቢኖር ኖሮ… ይህ ፍርድ ቤት ቢኖር ኖሮ ምናልባትም በትግራይ የተከሰተው ፍጅት አይከሰትም ነበር። የምርጫ መራዘም፣ የክልል በጀት መከልከል፣ እንዲሁም በሕገ-ወጥ መንገድ የብልጽግና ፓርቲ መመሥረት በሕግ እልባት ያገኙ ነበር።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች “የትግርኛ ተናጋሪ” በሚል በዶክመንተሪ ጥላቻ ሲቀሰቀስባቸው አቤቱታ የሚያቀርቡበት ገለልተኛ አካል አልነበረም። የብዙ ሕዝቦች የማንነትና የራስ-አስተዳደር ጥያቄ መታፈንም የፍርድ ቤቱን አስፈላጊነት ያሳያል።

ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች ሲቋቋሙ👇

  1. ሕገ-መንግሥቱን ይተረጉማሉ፤
  2. ከሕገ-መንግሥቱ ጋር የሚጋጩ ሕጎችን ይከላከላሉ፤
  3. የሕግ አስፈጻሚውን አካል በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲገደብ ያደርጋሉ።

በተለይ በሀገራችን ከብሔሮችና ሕዝቦች መብት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማስከበር የዚህ ተቋም መኖር አያጠያይቅም።

ስለዚህ የሚመለከተው የፖለቲካ አካልና ምሁራን ይህንን ሐሳብ ሊያዳብሩትና ተግባራዊ ሊያደርጉት ይገባል ሲሉ የ WT Media ተጋባዥ ጸሐፊ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ይጠቁማሉ።