GridArt_20260403_214524337

በአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር በ40 ሚሊዮን ብር የተገዛችውና ስድስት ወር ያልሞላት አዲስ የከንቲባ መኪና፣ ከንቲባ ዶክተር መስፍን ማንዛ ራሳቸው ያለመንጃ ፈቃድ ሲያሽከረክሩ በደረሰ አደጋ ክፉኛ መውደሟን የ WT Media የምርመራ ዘገባ አመለከተ።

አደጋውን ተከትሎ ለጥገና የተጠየቀውን 5 ሚሊዮን ብር የጋሞ ልማት ማህበር የአርባ ምንጭ ቅርንጫፍ እንዲከፍል ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተረጋግጧል።

የመረጃ ምንጮቻችን እንደጠቆሙት፣ አደጋው የደረሰው ከንቲባው ያለመንጃ ፈቃድ መኪናዋን ሲያሽከረክሩ ነው። መኪናዋ ከተጋጨች በኋላ ከከተማው ከጠፋች ከ10 ቀናት በላይ ተቆጥሯል።

ይህ መሰወር በአደጋው ዙሪያ ያለውን መረጃ ለመደበቅና ሕዝቡ እንዳያውቀው ለማድረግ የተደረገ ሴራ እንደሆነ ይታመናል።

ለ40 ሚሊዮን ብር መኪና ጥገና 5 ሚሊዮን ብር መጠየቁ በራሱ ከፍተኛ ዝርፊያ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ይህንን ወጪ የጋሞ ልማት ማህበር የአርባ ምንጭ ቅርንጫፍ እንዲሸፍነው ለማድረግ እየተሞከረ ነው።

የልማት ማህበሩ ገንዘብ ለከተማዋ ልማትና ለድሆች መርጃ መዋል ሲገባው፣ በአመራሮቹ ጥፋት ለወደመች መኪና ጥገና መባከኑ የሕዝብን አደራ መብላት እንደሆነ የዘገባችን ምንጮች ገልጸዋል።

ይህ አደጋ በአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር የተፈጸመ የመጀመሪያው አይደለም። ቀደም ብሎም፣ አቶ አብርሃም አምሳሉ የተባሉ የከተማዋ የፓርቲ አመራር ከአስተባባሪነት ኃላፊነታቸው ሲነሱ፣ በንዴትና ሰክረው ያለመንጃ ፈቃድ ሲያሽከረክሩ መኪና አጋጭተው ለጥገና 1.5 ሚሊዮን ብር እንደወጣ ይታወሳል።

ለ WT Media አስተያየት የሰጡ አንድ የትራፊክ ፖሊስ አባል እንደተናገሩት፣ ሁለቱም አደጋዎች የደረሱት አመራሮቹ መንጃ ፈቃድ ሳይኖራቸው ሲያሸከረክሩ ነው።

ይሁን እንጂ፣ አመራሮቹ ሥልጣናቸውን ተገን በማድረግ የሕግ ተጠያቂነትን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ላይ እንቅፋት እየፈጠሩ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህም በከተማዋ ያለውን የሕግ የበላይነት መላላትና የአመራሮቹን ተጠያቂነት ማጣት በግልጽ ያሳያል።

የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደርና የሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት በዚህ ጉዳይ ላይ አስቸኳይና ገለልተኛ ምርመራ እንዲያደርጉ WT Media በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገራቸው ተናግረዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎቹ “የሕዝብ ሀብት በባለሥልጣናት ኃላፊነት ማጣት እንዲባክን መፍቀድ ተቀባይነት የለውም፣ ጥፋተኞቹ በሕግ ሊጠየቁና የተባከነው ገንዘብ ወደ ሕዝብ ሊመለስ ይገባልም” ብለዋል።