በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በዎላይታ ሶዶ ከተማና አካባቢው የሚታየው የነዳጅ እጥረትና እንግልት፣ በአመራሮችና በስግብግብ ነጋዴዎች የተቀነባበረ የዝርፊያ መድረክ እየሆነ መምጣቱን WT Media አረጋግጧል።
የከተማዋ ነዋሪዎችና አሽከርካሪዎች “ገለልተኛ ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ካልተቋቋመ ዝርፊያው ወደ ከፋ ደረጃ ሊሸጋገር ነው” ሲሉ ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

በምርመራችን ወቅት እንደተረጋገጠው፣ ነዳጅ ለሕዝብ አገልግሎት ከሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ይልቅ ሥራ ላይ ለማይውሉ ለተመደቡ መኪኖች በስፋት እየተቀዳ እንዲሁም ተደብቆ ለህግ ወጥ ነጋዴዎች እንዲሸጥ እያደረገ ይገኛል።
እነዚህ መኪኖች ከማደያ የቀዱትን ነዳጅ ወዲያውኑ ለጭነት መኪና አሽከርካሪዎች በእጥፍ ዋጋ በመሸጥ ከፍተኛ ትርፍ እያጋበሱ መሆኑ ተረጋግጧል።
ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው፣ ይህ ሕገ-ወጥ ግብይት በስግብግብ ነጋዴዎች ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ አመራሮችና የተወሰኑ የፖሊስ አባላት ጥቅም ተጋሪ በመሆን ጭምር የሚመራ መሆኑ ነው።
እነዚህ ኃላፊዎች ችግሩን ከመፍታት ይልቅ፣ ሥልጣናቸውን ተገን በማድረግ ለግል ጥቅም መሯሯጣቸው ከሞራልና ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ ተግባር መሆኑን ታዛቢዎች ገልጸዋል።
የመረጃ ምንጮቻችን እንደጠቆሙት፣ በዚህ ሕገ-ወጥ የነዳጅ ንግድ ውስጥ በቀጥታ የሚሳተፉ አመራሮችን በስም መጥራት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ቢደረስም፣ ለጊዜው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ዕድል ተሰጥቷቸዋል።
ይሁን እንጂ ድርጊቱ የማይቆም ከሆነ WT Media የእነዚህን አመራሮች ማንነትና የስም ዝርዝር ይፋ የሚያደርግ ይሆናል።
አሁን ያለው የነዳጅ ቁጥጥር ሥርዓት ከዘራፊዎች ጋር የተቆራኘ በመሆኑ፣ ሕዝቡ የሚከተሉትን አስቸኳይ እርምጃዎች ይጠይቃል።
ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት የጸዳና በሕዝብ የታመነ ገለልተኛ የነዳጅ ተቆጣጣሪ ኮሚቴ በአስቸኳይ ተዋቅሮ ሥራ እንዲጀምር የሚለው አማራጭ እየተሰማ ይገኛል።
በተጨማሪም በማደያዎች አካባቢ የሚታየውን የፖሊስና የአመራር ጣልቃ ገብነት እንዲቆምና በነዳጅ ንግድ ላይ የተሰማሩ ስግብግብ ነጋዴዎችና አባሪዎቻቸው በሕግ እንዲጠየቁ በማለትም ህብረተሰቡ እያሳሰበ ነው።