GridArt_20260409_160941241

በዎላይታ ሶዶ ከተማና አካባቢው ለተከሰተው ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት፣ የጸጥታ አካላትና ከፍተኛ አመራሮች በቀጥታ ተሳታፊ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ አዳዲስ መረጃዎች ለ WT Media ደርሰዋል።

የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የኦፋ ወረዳ ፖሊስ አዛዥና የፓትሮል ሹፌር የፖሊስ ፓትሮል መኪናን በመጠቀም ከማደያዎች ነዳጅ ከቀዳ በኋላ ወዲያውኑ ለጭነት መኪናዎች በከፍተኛ ዋጋ ተገልብጦ እንደሚሸጥ ተደርሶባቸዋል።

በትናንትናው ዕለት ይሄ የፖሊስ ፓትሮል መኪናው ሁለት ዙር ነዳጅ ከዎላይታ ሶዶ ከተማ ከሚገኘው ማደያ በጃሪካን ጭምር ከቀዳ በኃላ ለሌላ ጭነት መኪና በመሸጥ ተጨማሪ ደግሞ ወደ ጉኑኖ ከተማ በማቅናት ከቀዳ በኃላ ዳግም ከዎላይታ ሶዶ ለመቅዳት ሲሞክር በዎላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ ክትትል እንደተደረሰበት ተገልጿል።

መረጃው እንደሚጠቁመው፣ በትላንትናው ዕለት የሶዶ ከተማ ፖሊስ ከዚሁ ነዳጅ ዝርፊያው ጋር በተያያዘ የፖሊስ ፓትሮል መኪናውንና አሽከርካሪውን ከእነ አዛዥ በቁጥጥር ስር አውሎ ነበር።

ሆኖም ግን የዞኑ ፖሊስ አዛዥ፣ በቁጥጥር ስር ውለው በዎላይታ ሶዶ ፖሊስ ጣቢያ እስረኞች ማረፊያ የገቡትን ግለሰቦችና መኪና ወደ ማታ አከባቢ ጫና በማድረግ በግዴታ እንዲፈቱ ማድረጉን አንድ የዎላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ አባል እና የአይን እማኝ ለ WT Media አስረድቷል።

በዚህ ህገወጥ ተግባር ተጠያቂነት አለመኖርና ጠልቃገብነት በህግ ማስከበር ተግባር ላይ ከፍተኛ ጭቅጭቅና አለመግባባት መፈጠሩም ታውቋል።

በምርመራው ወቅት እንደታወቀው፣ የአብዛኛው መዋቅር ፖሊስ መኪኖች ኮንትሮባንድ ንግድና በመሰል ህገወጥ ተግባር ተሰማርተው ከዞን፣ ከክልል ፀጥታ አመራሮች ጋር የጥቅም ተጋሪ ስለመሆናቸውም ጠቁመዋል።

WT Media ትናንት ባቀረበው ዘገባ፣ ሕዝቡ ገለልተኛ የቁጥጥር ኮሚቴ እንዲቋቋም መጠየቁ ይታወሳል።

አሁን የወጡት መረጃዎች ደግሞ ዘራፊዎቹና ተቆጣጣሪዎቹ አንድ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ በመሆናቸው፣ የሚመለከተው የክልልና የፌዴራል መንግሥት አካላት በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ ቀርቧል።

WT Media ጉዳዩን በቅርበት መከታተሉን የሚቀጥል ሲሆን፣ በቀጣይ የተሳታፊዎችን የስም ዝርዝርና ተያያዥ ማስረጃዎችን ይፋ እንደሚያደርግ ያሳውቃል።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media