በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ ዶ/ር መስፍን ማንዛ፣ ያለመንጃ ፈቃድና በስካር መንፈስ ሲያሽከረክሩ በ40 ሚሊዮን ብር የተገዛችውን አዲስ የቅንጦት መኪና አጋጭተው ማውደማቸውንና የጥገናውን 5 ሚሊዮን ብር ከሕዝብ መጠየቃቸውን የሚገልጽ መረጃ በማህበራዊ ሚዲያ መሰራጨቱን ተከትሎ፣ ወጣት ዮሴፍ ዮሐንስን አሳስረዋል።
ምንም እንኳ ወጣት ዮሴፍ ዮሐንስ ለ WT Media መረጃውን ያደረሰ ባይሆንም፣ ከንቲባው “መረጃውን አውጥተሃል” በሚል ጥርጣሬ ወጣቱን ከአርብ ሚያዝያ 2 ቀን 2018 ዓ.ም (2/8/2018) ጀምሮ አሳስረውታል።
ይህ ድርጊት የመረጃ ሰጪዎችን መብት የሚጥስና እውነትን ለማፈን የተደረገ ሕገ-ወጥ እስር መሆኑን WT Media ታዝቧል።
እንደ መረጃ ምንጮቻችን ገለጻ፣ ከንቲባ ዶ/ር መስፍን ማንዛ አደጋውን ያደረሱት ያለመንጃ ፈቃድና በስካር መንፈስ (Intoxication) መኪናውን በሚያሽከረክሩበት ወቅት ነው።
አደጋው የደረሰባት ነጭ ቶዮታ ላንድክሩዘር (Toyota Land Cruiser Prado) መኪና በቅርቡ በ40 ሚሊዮን ብር የሕዝብ ሀብት የተገዛች ነበረች።

ከንቲባው ያደረሱትን የ5 ሚሊዮን ብር የጥገና ወጪ ከሕዝብ በጀት ማለትም ከጋሞ ልማት ማህበር አርባምንጭ ቅርንጫፍ እንዲሸፈን መጠየቃቸውም ታውቋል።
ወጣት ዮሴፍ ዮሐንስ (በምስሉ ላይ የሚታየው) ለሚዲያ መረጃውን ያደረሰው ግለሰብ ባይሆንም፣ በአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ እንዲታሰር መደረጉ፣ አመራሩ በክልሉ ውስጥ ያለውን ነፃ የሐሳብ ልውውጥና ተጠያቂነትን ለመግታት ያለውን ፍላጎት ያሳያል።
ፖሊስ ከንቲባው በሕዝብ ሀብትና በደኅንነት ላይ ያደረሱትን ጥፋት ከመመርመር ይልቅ፣ ንጹሕ ዜጋን በማሳሰር የከንቲባው መጠቀሚያ መሆኑ ተገልጿል።
የመረጃው ምንጭ የታሰረው ግለሰብ ባይሆንም፣ ማንኛውም ዜጋ በሕዝብ ሀብት ላይ የሚፈጸምን ዝርፊያና ጥፋት የማጋለጥ መብት አለው።
በመሆኑም ወጣት ዮሴፍ ዮሐንስ “መረጃ አውጥተሃል” በሚል ሰበብ የታሰረ በመሆኑ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈታ፤ የፌዴራልና የክልሉ ፍትሕ አካላት በከንቲባው የሙስናና የሕግ ጥሰት ላይ ገለልተኛ ምርመራ እንዲያደርጉ እንዲሁም የሕዝብ ሀብት ለባለሥልጣናት ስካርና ብክነት መዋል እንዲያቆም የመረጃ ምንጮች እየጠየቁ ይገኛሉ።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media