የዎላይታ ዞን ፖሊስ “በዞኑ የፖሊስ አዛዡ፥ የፖሊስ ፓትሮል መኪና በመጠቀም ነዳጅ ከየማዳያው እየቀዳ እየሸጠ በህግ ቁጥጥር ስር ዋለ” የሚለውን የ WT Media ዘገባ የዞኑ ፖሊስ መምሪያ “የበሬ ወለደ” ወሬ ሲል በመግለጫው አስተባብሏል።
ከሶስት ቀናት በፊት WT Media ይፋ ባደረገው የምርመራ ዘገባ፣ የሕግ አስከባሪው አካል ራሱ የሕገ-ወጥ ድርጊቱ ዋነኛ ተዋናይ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎችን አቅርቦ ነበር።
በዘገባው የኦፋ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ረ/ኢ/ር ዘገዬ ዛካሪያስ እና አሽከርካሪያቸው የፖሊስ ፓትሮል መኪናን እንደ ሽፋን በመጠቀም ከማደያዎች በጃሪካን ነዳጅ ሲቀዱ መቆየታቸው።
ነዳጁ ከመንግሥት ማደያ በሕጋዊ ዋጋ ከተቀዳ በኋላ፣ ወዲያውኑ ለጭነት መኪናዎች በውድ ዋጋ “በጥቁር ገበያ” እንደሚሸጥ ተደርሶበታል።
የሶዶ ከተማ ፖሊስ እነዚህን ግለሰቦች እጅ ከፍንጅ ይዞ በማረፊያ ቤት ቢያቆይም፣ የዞኑ ፖሊስ አዛዥ በፈጠሩት ከፍተኛ ጫና እስረኞቹ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ መደረጉን የአይን እማኞች አረጋግጠዋል።
ይህ ዘገባ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን መቀስቀሱን ተከትሎ፣ የዎላይታ ዞን ፖሊስ መምሪያ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ዘገባውን “የሀሰት ውንጀላ” ሲል ፈርጆታል።
የመምሪያው መከላከያ ነጥቦች፥ የኦፋ ወረዳ ፖሊስ መኪና በወቅቱ የነበረው በጋራዥ ውስጥ እንደሆነና የመኪናው ታንከሩ ቱቦ በመዘጋቱ ቆሻሻና ውሃ ሲወጣለት እንጂ ነዳጅ ሲሸጥ እንዳልነበረ ገልጿል።
በወቅቱ በሶዶ ከተማ ፖሊስና በወረዳው ፖሊስ መካከል የተፈጠረው ሁኔታ “በመግባባት የተፈታ” መሆኑንና ምንም ዓይነት እስር እንዳልነበረ መምሪያው ይከራከራል።
መምሪያው ይህንን ዘገባ ያሰራጨው የ WT Media ባለቤትና “የውስጥ ባንዳዎች” ላይ ምርመራ ጀምሬ ለሕግ አቀርባለሁ ሲል ዝቷል።
ምንም እንኳን ፖሊስ መምሪያው ድርጊቱን ቢያስተባብልም፣ በዘገባውና በመግለጫው መካከል ያሉ ተቃርኖዎች አሁንም አሳማኝ መልስ ይሻሉ።
መረጃው ከወጣ ከሶስት ቀናት በኋላ መግለጫ መሰጠቱና በውስጥ የመረጃ ምንጮች የተጠቆመው “የአዛዦች አለመግባባት” ለምን እንዳልተጠቀሰ ጥርጣሬ ፈጥሯል።
ነዋሪዎችና አሽከርካሪዎች በማደያዎች አካባቢ የሚታየውን የአመራሮችና የፖሊስ ጣልቃ ገብነት በግልጽ እያወገዙ ባሉበት ወቅት፣ የፖሊስ መምሪያው መከላከያ ምን ያህል አሳማኝ ሊሆን ይችላል? የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነው።
WT Media የሕዝብን ብሶትና የመረጃ ምንጮቹን ዋስትና በጠበቀ መልኩ ዘገባውን ማቅረቡን ይቀጥላል። የዛሬው የፖሊስ መግለጫ የነዳጅ እጥረቱን ከመፍታት ራሱን ከማረም ይልቅ ጋዜጠኞችንና የመረጃ ምንጮችን በማስፈራራት ላይ ማተኮሩ አሳዛኝ መሆኑን እንገልጻለን።
የነዳጅ ዘረፋው ሰንሰለትና ተሳታፊዎችን በተመለከተ የደረሱን ተጨማሪ ምስላዊ መረጃዎችንና የሰነድ ማስረጃዎችን በቀጣይ ለሕዝብ ይፋ እንደምናደርግ እናሳውቃለን።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media