በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጎፋ ዞን የጋልማ ከተማ አስተዳደር የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ያስተላለፈውን የውሳኔ ትዕዛዝ ተግባራዊ አላደርግም ማለቱን ተከትሎ፣ በከተማዋና በዛላ ወረዳ ስር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች መማር ማስተማር ሙሉ በሙሉ መቆሙ ታውቋል።
መምህራኑ የአስተዳደሩን ድርጊት “ሕገ-ወጥና አስተዳደራዊ በደል” ሲሉ ለ WT Media በላኩት መረጃ እና ማስረጃ ኮንነዋል።
በአቶ ግርማ ወዜ የሚመሩ 125 መምህራንና የመንግሥት ሠራተኞች ላቀረቡት አቤቱታ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በቁጥር ዕንባ/ሀቅ/171/120/08439 በቀን **27/05/2018 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ መፍትሔ እንዲሰጥ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።

ሠራተኞቹ ያቀረቧቸው መሠረታዊ የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች፦ ከሕግ አግባብ ውጭ የተከለከለ የ9 ወር ውዝፍ ክፍያ፣ ከ2013 እስከ 2017 ዓ.ም የተከማቸ የደረጃ ዕድገትና የትምህርት ማሻሻያ ውዝፍ ክፍያ እና የ2017 ዓ.ም የኑሮ ውድነት ማካካሻ (የጥቅምት ወር ክፍያ)።
በተጨማሪም በ2017 ዓ.ም ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ቦንድ የተቆረጠ ገንዘብ ተመላሽ፣ የ2018 ዓ.ም አዲሱ የደመወዝ ጭማሪ የመስከረም ወር ውዝፍ መሆኑን ለ WT Media ገልጸዋል።
የዕንባ ጠባቂ ተቋም ምርመራውን ካጠናቀቀ በኋላ፣ ጋልማ ከተማ አስተዳደር እስከ መጋቢት 30/2018 ዓ.ም ድረስ ክፍያውን ፈጽሞ ሪፖርት እንዲያደርግ በ30 የሥራ ቀናት ገደብ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
ይሁን እንጂ አስተዳደሩ ትዕዛዙን ባለመቀበል ክፍያውን ባለመፈጸሙ፣ በጋልማ ከተማና በዛላ ወረዳ የሚገኙ መምህራን በወሰዱት የሥራ ማቆም እርምጃ መማር ማስተማር መቋረጡን ከቦታው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የጋልማ ከተማ መምህራን ማኅበር በበኩሉ፣ መምህራን ጥቅማቸው ተከብሮ በሰላም ወደ ሥራ እንዲመለሱ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም ከአስተዳደሩ ተገቢውን ምላሽ አላገኘም።
ማኅበሩ በጻፈው ደብዳቤ፣ “መምህራን በኑሮ ውድነትና በአስተዳደራዊ በደል እየተጎዱ መማር ማስተማር መቀጠል አይቻልም” ሲል አስታውቋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የሚመለከታቸውን አካላት ምላሽ ለማካተት ያደረግነው ጥረት ባይሳካልንም ይህ የአስተዳደር አካላት የሕግ የበላይነትን የመናቅና የዜጎችን መሠረታዊ መብት የመርገጥ ተግባር በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል።
የጎፋ ዞንና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጉዳዩን በትኩረት ተመልክተው መፍትሔ እንዲሰጡና የተቋረጠው መማር ማስተማር እንዲቀጥል እናሳስባለን።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media