በተደጋጋሚ የሚሰጥ የቀጠሮ መራዘም ለአለልኝ አዘነ ቤተሰቦች ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራና የሥነ-ልቦና ስብራት እየሆነባቸው ይገኛል

የታዋቂው የባህር ዳር ከተማና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አለልኝ አዘነ የግድያ መዝገብ ላይ ዛሬ ሚያዝያ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ ይዞ የነበረው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዎላይታ ምድብ ችሎት፣ ቀጠሮውን ለአንድ ወር በማራዘም ለግንቦት 13 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል።

ለዛሬው የውሳኔ ቀጠሮ በርካታ የሟች አለልኝ አዘነ ቤተሰቦች ትናንት ከአርባ ምንጭና ከተለያዩ አካባቢዎች ተሰባስበው ትናንት ምሽት ዎላይታ ሶዶ የገቡ ቢሆንም፣ ቀጠሮው መራዘሙ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ፈጥሮባቸዋል።

 ቤተሰቦቹ ለ WT Media ባደረሱት ቅሬታ እንደገለጹት በሀገሪቱ ባለው የነዳጅ እጥረትና የትራንስፖርት ውድነት ምክንያት ለእያንዳንዱ ሰው እስከ አንድ ሺህ ብር እየከፈሉ ከአርባ ምንጭ ወደ ዎላይታ ሶዶ መጓዛቸውን ገልጸዋል።

ቤተሰቦቹ ትናንት ምሽት ዎላይታ ሶዶ ከተማ በመግባት አልጋ ይዘው ያደሩ ቢሆንም፣ ዛሬ ጠዋት ወደ ፍርድ ቤት ሲያመሩ መዝገቡ በዕለቱ ቀጠሮ ላይ አለመለጠፉን አረጋግጠዋል።

ቤተሰቦቹ እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ ፍርድ ቤት ቢጠባበቁም፣ መዝገቡ በዕለቱ የችሎት ዝርዝር ውስጥ ሳይካተት መቅረቱ ለከፍተኛ ድካምና እንግልት ዳርጓቸዋል።

“መዝገብ ጠፍቷል እየፈለግን ነው እያሉ” ከቆዩ በኃላ ከበርካታ ሰዓት መጠበቅ በኃላ በድጋሚ ለአንድ ወር በማራዘም ለግንቦት 13 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱንም ጠቅሷል።

ይህ በተደጋጋሚ የሚሰጥ የቀጠሮ መራዘም በሟች ቤተሰቦች ላይ ከባድ የሥነ-ልቦና ጫና እየፈጠረ ይገኛል። 

ቤተሰቦቹ “ዳኞቹ እርስ በእርስ አልተስማሙም” በሚል ምክንያት ቀጠሮው ለአንድ ወር መራዘሙን እንደሰሙ በመግለጽ፣ ይህም በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጡ እያደረጋቸው መሆኑን በዕንባ የታጀበ ድምፃቸውን አሰምተዋል።

ቤተሰቦቹ መዝገቡ ከአርባ ምንጭ ወደ ዎላይታ መዛወሩንና የሚሰጡትን ቀጠሮዎች “ፍትሕን ለማድበስበስ የታሰቡ ሴራዎች ናቸው” ሲሉ ይከሳሉ።

 በግድያ ወንጀሉ ጥፋተኛ ተብላ በጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ16 ዓመት ጽኑ እስራት የተፈረደባት የአደይ ጌታቸው እናት፣ የወቅቱ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የቅርብ ዘመድ መሆናቸው በሂደቱ ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው የሚል ስጋት አላቸው።

ቤተሰቡ “ይህ በዝምድና ፍትሕን የማጣመም ሴራ ነው” ሲሉ ድምፃቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።

WT Media ጉዳዩን በቅርበት መከታተሉን የሚቀጥል ሲሆን፣ የሕዝብ ባለውለታ ለነበረው አለልኝ አዘነ ቤተሰቦች የሚገባቸው ፍትሕ ያለምንም ዝምድናና ተጽዕኖ በአፋጣኝ እንዲሰጥ ያሳስባል።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media