የኦሞ ወንዝ ሙላት በዳሰነች ወረዳ ከፍተኛ ውድመት እያደረሰ ነው፤ ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተሳሰበ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዳሰነች ወረዳ የኦሞ ወንዝ በከፍተኛ ፍጥነት በመሙላቱ ምክንያት በአካባቢው ሰብሎች፣ መሠረተ ልማቶችና የእርሻ መሬቶች ላይ ከባድ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተገለጸ።

የዘንድሮው የኦሞ ወንዝ ሙላት ከወትሮው በተለየ ፍጥነት እየጨመረ በመሆኑ በአካባቢው ላይ ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል። እስካሁን በደረሰው መረጃ መሠረት  በአካባቢው በስፋት ተዘርቶ የነበረው የበቆሎ እርሻ በወንዙ ሙላት ሙሉ ለሙሉ በውኃ በውኃ ተውጧል።

ወንዙ ከመጠን በላይ በመሙላቱ ምክንያት በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት፣ መንገዶችና ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል። ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች በጎርፍ በመሸፈናቸው አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ለከፍተኛ ኪሳራ ተዳርገዋል።

የወንዙ ሙላት በየሰዓቱ እየጨመረ በመሆኑ፣ በወንዝ ዳርቻ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሊፈጠር የሚችለውን የከፋ አደጋ ለመከላከል በከፍተኛ ንቃት አካባቢያቸውን እንዲቃኙና አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ WT Media ያሳስባል።

በዳሰነች ወረዳ እየደረሰ ያለው ይህ የተፈጥሮ አደጋ አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍና የመንግሥትን ትኩረት የሚሻ ነው። በተለይም በጎርፍ ምክንያት ለተፈናቀሉና ሰብላቸው ለወደመባቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲደረግ እናሳስባለን። ጉዳዩን በቅርበት በመከታተል ተጨማሪ መረጃዎችን የምናደርስ ይሆናል።