GridArt_20260504_171340085

በ21ኛው ክፍለ ዘመን፣ ዓለም በቴክኖሎጂ በረቀቀችበት ወቅት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ዜጎች ግን ዛሬም የታመመ ወገናቸውንና ምጥ የያዛቸውን እናቶችን በቃሬዛ ተሸክመው በዱር በገደሉ ለሰዓታት ይጓዛሉ።

ይህ ዘገባ በክልሉ በተለይም በጎፋና በቡርጂ ዞኖች ያለውን አሳዛኝ እውነታና የመንግሥትን ግድየለሽነት በጥልቀት ይፈትሻል።

ከሦስት ወራት በፊት WT Media ሕዝቡ በራሱ አቅም የእንጨት ድልድይ ሠርቶ እናቶችን እያሻገረ መሆኑን መዘገቡ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ባለፈው ሚያዝያ 23 ቀን 2018 ዓ.ም. በቡርጂ ዞን በአራቱ ቀበሌያት (ቦንጮ፣ አራሻ፣ ሚስሞ እና በነያ) ሕዝብ ጥረት ተገንብቶ የነበረው የባጋዴ ድልድይ በከባድ ጎርፍ ተወስዷል።

የእንጨት ድልድይ እየገነቡ – አሁን በጎርፍ ተወስዷል
ድልድይ በመሰበሩ ሞቶር ተሸክሞ ማሻገር
ወላድ እናት በሞተር ሳይክል እየተጓዘች

ሚያዝያ 24 ቀን በቤቷ ያለ ባለሙያ እርዳታ የወለደች እናትና ሕፃን ልጇ በሞትና በሕይወት መካከል ሆነው በሞተር ሳይክል ወደ ሶያማ ሆስፒታል ቢደርሱም፣ “አምቡላንስ የለም” በሚል ሰበብ ለሰዓታት ደጅ እንዲጠኑ ተደርገዋል። በመጨረሻም ህይወት ሊያልፍ ችሏል።

አምቡላንስ በማጣት ልጇ የሞተባት

የቦንጮ ሕዝብ ድምፁን በማሰማቱ ብቻ፣ የዞኑ አመራሮች “ስማችንን በሚዲያ አዋረዳችሁ” በሚል ቂም በመያዝ፣ ከክልል ተመድቦ የነበረውን የጤና ጣቢያ ግንባታ ዕድል ሆን ብለው ወደ ሌላ አካባቢ እንዳዛወሩት ነዋሪዎች በምሬት ይገልጻሉ።

መንገድ ላይ ወላድ እናት ሚጥ ላይ

በጎፋ ዞን ደግሞ ጉዳዩ የባሰ ነው። ለተጎጂዎች የተሰበሰበ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ የት እንደገባ ሳይታወቅ፣ በገዜ ጎፋ ወረዳ ያለውን ብቸኛ አምቡላንስ ለሽያጭ ጨረታ ማውጣቱ ሕዝቡን አስቆጥቷል” የሚለውን ከሶስት ቀን በፊት መዘገባችን ይታወሳል።

ከወር በፊት በውዘቴ በደረሰ አደጋ አንዲት ወጣት በአምቡላንስ ዕጦት ሕይወቷ ማለፉ ቢታወቅም፣ አስተዳደሩ ግን ያለውን ንብረት ከመጠገን ይልቅ ለመሸጥ መወሰኑ “በሕዝብ ሕይወት መቆመር ነው” ተብሏል።

የክልሉ ፕሬዝዳንት ጥላሁን ከበደ  “ኦቶናን እናክመው” ብለው ጥሪ ካስተላለፉ አንድ ዓመት ሊሞላው ቢሆንም፣ እስካሁን ግንባታው አልተጀመረም። ምስኪን ዜጎች በግል ጤና ተቋማት ለመታከም አቅም አጥተው ለሞት እየተዳረጉ ነው።

በክልሉ ለድንገተኛ አደጋ የተመደቡ አምቡላንሶች ለባለሥልጣናት የግል ጉዳይና ለቢሮ ሥራዎች መገልገያ እየዋሉ መሆኑን የደረሱን መረጃዎች ያረጋግጣሉ። 

ሪፖርቶች እናቶችን በቃሬዛ መሸከም መቀነሱን ቢገልጹም፣ በመሬት ላይ ያለው እውነታ ግን እናቶች በአደገኛ የእንጨት ድልድዮች ላይ በወጣቶች ትከሻ ተጭነው ለሞት ይዳረጋሉ።

WT Media በእነዚህ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ከጎፋ ዞን፣ ከቡርጂ ዞንና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት አድርጓል።

ሆኖም ግን ኃላፊዎቹ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የሕዝቡን ብሶትና የእኛን ጥያቄ ሳይመለሱ ቀርተዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ትኩረቱ በውስጥ ሽኩቻና በጥቅም ትስስር ላይ ሳይሆን፣ በሕዝብ ደኅንነት ላይ ሊሆን ይገባል።

የእናቶች ሞት የሚቀነሰው በወረቀት ላይ በሚጻፍ ሪፖርት ሳይሆን፣ እናቶች በቃሬዛ የሚሸከሙበትን መንገድና ድልድይ በመገንባት ነው።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ለአምቡላንሶች አግባብ ያልሆነ አጠቃቀም ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርግና ለገጠራማው ሕዝብ የጤና ተቋማት እና የመንገድ ግንባታዎች ቅድሚያ እንዲሰጥ WT Media በጥብቅ ያሳስባል።

ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን!

Voice of Marginalized Community – WT Media