ለእናቶች ሞት ምክንያት የሆነው የመንገድ እጦት – የአስተዳደሩ ጆሮ ዳባ እና የሕዝቡ ሰቆቃ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን፣ በሆብቻ ወረዳ የሚገኘው የጭፍሳ ቀበሌ ነዋሪዎች፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዛሬም ድረስ በመሠረታዊ የመንገድ መሠረተ ልማት እጦት ምክንያት ለከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መጋለጣቸውን ለ WT Media ገለጹ።

በተለይም “ይናፌ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች፣ የታመሙ ወገኖቻቸውንና ምጥ የያዛቸውን እናቶችን ወደ ጤና ተቋም ለማድረስ የሚጓዙበት መንገድ “የሞት መንገድ” እየሆነባቸው ይገኛል።

ጭፍሳ ቀበሌን ከወረዳው ማዕከል ጋር የሚያገናኝ የመንገድ መሠረተ ልማት ባለመኖሩ፣ ነዋሪዎች የሰው ኃይልን በመጠቀም በቃሬዛ ተሸክመው ረጅም ርቀት ለመጓዝ ይገደዳሉ። WT Media የተመለከተው የቪዲዮ ማስረጃ እንደሚያሳየው፣ ወጣቶችና ጎልማሶች በመንገድ እጦት የሞተውን፣ የታመመውን ሰው እንዲሁም ወላድ እናቶችን በቃሬዛ ተሸክመው ድንጋያማና ዳገታማ በሆኑ መንገዶች ላይ ሲጓዙ ይታያሉ።

ከዚህም በላይ፣ በአካባቢው የሚገኘውንና እጅግ አስቸጋሪ የሆነውን የብሣሬ ወንዝ በእግር ተሸክሞ መሻገር የግድ ይላል። ይህ ጉዞ ለጤናማ ሰው እንኳን እጅግ አድካሚ ቢሆንም፣ ነፍሰ ጡር እናቶችና አስቸኳይ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች ግን በዚህ ስቃይ ውስጥ እንዲያልፉ መደረጋቸው በእናቶችና በሕፃናት ሕይወት ላይ ከፍተኛ የሞት አደጋ እያደረሰ ይገኛል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ለ WT Media እንደገለጹት፣ ችግሩን በተደጋጋሚ ለሚመለከታቸው የወረዳና የዞን አመራሮች ቢያሳውቁም እስካሁን የተገኘ መፍትሔ የለም። “አመራሮቹ መጥተው ችግሩን አይተውና ቃል ገብተው ይሄዳሉ፤ ነገር ግን ድርጊቱ ከመሬት አይወርድም” በማለት ነዋሪዎቹ በምሬት ይገልጻሉ።

መንግሥት በየመድረኩ ስለ “እናቶች ሞት መቀነስ” እና “የመሠረተ ልማት ተደራሽነት” ቢሰብክም፣ በጭፍሳ ቀበሌ ያለው እውነታ ግን ከዚህ በተቃራኒው መሆኑ የአስተዳደሩን ቸልተኝነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።

የመንገድ እጦቱ ከጤና ችግር ባሻገር የአካባቢውን ምርት ወደ ገበያ ለማውጣት እንቅፋት ሆኗል። አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት በትከሻው ተሸክሞ ረጅም መንገድ መጓዝ ስላለበት፣ ለድካምና ለዝቅተኛ ገቢ ተዳርጓል። ይህ ደግሞ በአካባቢው ያለውን የኑሮ ሁኔታ ይበልጥ አክብዶታል።

በሆብቻ ወረዳ ጭፍሳ ቀበሌ የሚታየው ይህ አሳዛኝ ምስል፣ በክልሉ ያለውን የመሠረተ ልማት ክፍተትና የአመራሩን ግድየለሽነት ማሳያ ነው። WT Media ጉዳዩ የሚመለከተው የሆብቻ ወረዳ አስተዳደር፣ የዎላይታ ዞንና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ለዚህ ሕዝብ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ በጥብቅ ያሳስባል።