GridArt_20260510_162845008

​የዎላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በዛሬው ዕለት በተረጋገጠ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጠበላን ከሁምቦና አበላ አባያ የሚያገናኘው መንገድ ግንባታ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር (ERA) በይፋ መጀመሩን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ WT Media ከመሥሪያ ቤቱ ባደረገው ማጣራት ግን መግለጫው ከእውነት የራቀ ውሸት ሆኖ አግኝቶታል።
​
​ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በፌስቡክ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት “ከጠበላ ጀምሮ ሁምቦ ወረዳ ኤላ ቀበሌን አቋርጦ አበላ አባያ ወረዳን የሚያገናኘው መንገድ ግንባታ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር (ERA) ጀምሯል” ብለዋል።

አክለውም መንገዱ የሦስቱ መዋቅሮች የዘመናት የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ የቆየ መሆኑንና ዛሬ ምላሽ በማግኘቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አስተዳዳሪው ለዚህ ንግግራቸው እንደ ማሳመኛና ማረጋገጫ ይረዳ ዘንድ፣ በመንገዱ ላይ ሥራ እንደጀመሩ የሚያሳዩ ጥቂት ማሽኖችን (ግሬደሮችን) በሥፍራው አስገብተው በምስል አሳይተዋል።

WT Media የአስተዳዳሪውን መግለጫ ተከትሎ መረጃውን ለማረጋገጥ የፌዴራል ተቋም ወደሆነው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር (ERA) የስልክ ጥሪ በማድረግና ይፋዊ መረጃዎችን በመፈተሽ የሚከተሉትን እውነታዎች አረጋግጧል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የመሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለ WT Media እንደገለጹት፤ “የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር (ERA) ስለዚህ ግንባታ የሚያውቀው ምንም ዓይነት መረጃ የለም” ብለዋል።

እንደ ERA አሠራር ማንኛውም የፌዴራል መንገድ ግንባታ ሲጀመር በተቋሙ ድረ-ገጽ (Website) እና ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ መረጃው ለሕዝብ ግልጽ ይደረጋል። ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ ስለዚህ ፕሮጀክት የተባለ ምንም ነገር የለም።

ERA ፕሮጀክቱን እንደማያውቀው በገለጸበት ሁኔታ፣ በሥፍራው የገቡት ጥቂት ማሽኖች የማን ናቸው? የሚለው ትልቅ ጥያቄ አስነስቷል።

በአካባቢው ያሉ አንዳንድ ወገኖች እንደሚጠቁሙት፣ ማሽኖቹ ሕዝቡን ለማሳመንና “ሥራ ተጀመረ” የሚል ስሜት ለመፍጠር ብቻ የቀረቡ ሊሆኑ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

​የዞኑ አስተዳዳሪ የፌዴራል መሥሪያ ቤቱ “ጀመረ” ያሉትን ፕሮጀክት ራሱ መሥሪያ ቤቱ “አላውቅም” ማለቱ በአስተዳዳሪው መግለጫ ላይ ትልቅ ጥያቄ አስነስቷል።
​
​ሕዝቡን ለዘመናት ሲያሳቅቅ የቆየውን የመሠረተ ልማት ጥያቄ “ምላሽ አገኘ” ብሎ መግለጽ ተገቢ ቢሆንም፣ መሬት ላይ የሌለና የሚመለከተው አካል የማያውቀውን ግንባታ እንደተጀመረ አድርጎ መግለጽ ግን ሕዝብን ማታለልና የተሳሳተ ተስፋ መስጠት ነው ሲሉ አንድ የአከባቢው ተወላጆች ለ WT Media ተናግረዋል።

​እንዲህ ያሉ በባለሥልጣናት የሚሰጡ ያልተረጋገጡ መረጃዎች በኅብረተሰቡና በመንግሥት መካከል ያለውን መተማመን ይበልጥ ያሻክራሉም ብለዋል።

WT Media የዎላይታ ዞን አስተዳደር ስለዚህ የተጋጨ መረጃ ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥና ለሕዝቡ እውነተኛውን መረጃ ይፋ እንዲያደርግ ይጠይቃል።

​🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media