“ለጋዜጠኛ ምላሽ የማይሰጥ አካል ለህዝብስ እንዴት ምላሽ ይሰጣል?”
WT Media የጋዜጠኝነት ስነ-ምግባርን እና የህዝብን የመረጃ ማግኘት መብት መሰረት በማድረግ፣ በቅርቡ የተመሰረተውን የአማራ ፋኖ አንድነት እንቅስቃሴን በቅርበት ሲከታተል ቆይቷል። ማንኛውም የሀገርን መጻኢ እድል ለመወሰን እና “ለህዝብ እታገላለሁ” ብሎ የሚነሳ አካል ለገለልተኛ ሚዲያ እና ለህዝብ ግልጽና ተጠያቂ መሆን አለበት ብለን እናምናለን።
ባለፉት ጥቂት ወራት WT Media ከዚህ በፊት በየጊዜው ስለ ፋኖ ታጣቂ እንቅስቃሴ በተመለከተ ካቀረቧቸው ዘገባዎች በተጨማሪ ቀጥታ ከፋኖ አደረጃጀቱ አመራሮች ጋር ለመገናኘት እና ስለ ትግሉ አቅጣጫ ማብራሪያ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አድርጓል።
የፋኖ ከመገናኛ በዙኃን አስተባባሪው አቶ እዮብ ጥላሁን ጋር በተደረገ ግንኙነት መጀመሪያ ላይ ወደ ጋዜጣዊ መግለጫ ተጋብዘን የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ላይ ግን ያለ ምንም በቂ ምክንያት ከመድረኩ እንድንገለል ተደርጓል።
ይህም ሆኖ፣ WT Media አመራሮቹ አቋማቸውን በጽሁፍ እንዲገልጹ እና ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጡ ጥር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ዝርዝር መጠይቆችን አዘጋጅተን በኢሜል እና በዋትስአፕ ልኮ ነበር።
ይሁን እንጂ የሰጠናቸው ተደጋጋሚ የጊዜ ገደቦች ቢያልፉም፣ ምላሽ እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ለወራት ጥሪ ቢናደርግም አመራሮቹ እስካሁን ድረስ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
WT Media ግልጽነትን ለማስፈን እና የህዝብን የመጠየቅ መብት ለማክበር ሲል፣ ለአመራሮቹ የቀረቡትን እና እስካሁን ምላሽ ያልተሰጠባቸውን 4 መሰረታዊ ጥያቄዎችን እንደሚከተለው ለህዝብ ይፋ ያደርጋል።
1. ስለ ሃሳብ ልዩነት እና የውስጥ አንድነት
“የሃሳብ ልዩነት ተፈጥሯዊ ጸጋ ቢሆንም፣ በሀገራችን ፖለቲካ ግን ልዩነትን እንደ ጠላትነት የመፈረጅ አባዜ ስር የሰደደ ነው። እናንተም ወደ አንድነት ለመምጣት ረጅም ጊዜ ወስዶባችኋል። አሁን የተፈጠረው አንድነት ከሴራ፣ ከሀሰት ፕሮፓጋንዳ እና ከጸረ-ዲሞክራሲያዊ አካሄድ የጸዳ ለመሆኑና ነገ የተለየ ሃሳብ የሚያስተናግድ ለመሆኑ ምን ዋስትና አለ?”
2. ስለ ስልጣን ባለቤትነት እና የትግሉ ግብ
”ትግላችሁ በለስ ቀንቷችሁ ወደ ስልጣን ቢመጣ፣ ካለፉት ስርአቶች (ደርግ፣ ኢህአዴግ፣ ብልጽግና) በተለየ ምን አዲስ ውጤት ያመጣል? ፋኖ የሚታገለው ራሱ ስልጣን ለመያዝ ነው ወይስ ስልጣንን ለሀገሪቱ ባለቤት ለሆነው ለኢትዮጵያ ህዝብ ለማስረከብ? የሽግግር ሂደታችሁና የስልጣን ርክክብ ፍልስፍናችሁ ምን ይመስላል?”
3. ስለ ሀገራዊ አካታችነት እና ብሄር ብሄረሰቦች
”ፋኖ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ከ86 በላይ ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ያለው አመለካከት ምንድነው? ሁሉም ብሄር የየራሱን ማንነትና እሴት እኩል እንዲያሳድግ ትደግፋላችሁ? ትግላችሁ ‘ሀገራዊና የጋራ ነው’ የሚል አቋም ሌሎች ብሄሮች እንዲይዙ ያደረጋችሁት ተጨባጭ ስራ አለ? ከሰሜን ኢትዮጵያ አልፎ ወደ ደቡብና ሌሎች ክፍሎች ትግሉን ለማቀጣጠል ያላችሁ እስትራቴጂ ምንድነው?”
4. ስለ ሰብዓዊ ቀውስ እና የትግሉ ማብቂያ
”በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ቀርተዋል፤ እናቶችና ህሙማን መድሃኒትና መሰረታዊ አገልግሎት እያጡ ነው። እነዚህ ከህዝብ እለታዊ ኑሮ ጋር የተያያዙ ስራዎች እንዳይከናወኑ በፋኖ በኩል የሚደረጉ ክልከላዎች አሉ? ካሉስ ለምን? ትግሉን በተጨባጭ እቅድ መቼ አጠናቅቃችሁ ለህዝቡ እረፍት ትሰጣላችሁ? ሂደቱን በሰላም ለመቋጨት ያላችሁ ዝግጁነት ምን ያህል ነው?”

ከላይ ለቀረበው መሠረታዊ ጥያቄዎች የአመራሮቹ ዝምታ በህዝቡ ዘንድ ትልቅ ክፍተትን ይፈጥራል። WT Media እንደ ገለልተኛ የሚዲያ ተቋም የሁሉንም ወገን ሃሳብ ለማስተናገድ ያለውን ቁርጠኝነት እየገለጸ፣ አመራሮቹ ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለመስጠት ከወሰኑ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን።
እስከዚያው ግን ለነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ አለመስጠት በራሱ ትልቅ የፖለቲካ መልእክት እንዳለው እንገነዘባለን። በተጨማሪም “ለጋዜጠኛ ምላሽ የማይሰጥ አካል ለህዝብስ እንዴት ምላሽ ይሰጣል?” የሚለው ጥያቄ የህዝብ ሆኖ ይቆያል።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media