GridArt_20260514_183755067

​በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጋሞ ዞን አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ በሚገኙ የዘይሴ አካባቢዎች የመማር ማስተማር ሂደት ሙሉ በሙሉ ከተቋረጠ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል።

የዘይሴ ብሔረሰብ ሕገ-መንግሥታዊ የሆነ የግል መዋቅር ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ፣ በዞኑ አመራሮች የበቀል እርምጃ እየተወሰደበት መሆኑንና ይህም በትውልዱ መጻኢ ዕድል ላይ ከፍተኛ አደጋ መደቀኑን WT Media ያሰባሰባቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

​በአካባቢው የሚገኙ ከ10 በላይ ትምህርት ቤቶች ለአገልግሎት ዝግ ከሆኑ ሁለት ዓመታት ያለፉ ሲሆን፣ አብዛኞቹ በትጥቅ ኃይሎች እንደ ጦር ካምፕ እያገለገሉ ይገኛሉ።

WT Media ያገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ትምህርት ቤቶቹ ብቻ ሳይሆኑ የአካባቢው ጤና ጣቢያም ሳይቀር ለፀጥታ ኃይሎች ማረፊያነት ውለዋል።

​ዝግ ከሆኑት ትምህርት ቤቶች መካከል ዘይሴ አልጎ ፋንጎ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት፣​ ዘይሴ ኤልጎ ጎንቶ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ​ዘይሴ ኤልጎ ጎንቶ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት፣ ​ዘይሴ ወዘቄ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ​ዘይሴ ወዘቄ ሃውሻ ት/ቤት (ሙሉ በሙሉ በእሳት የወደመ)፣ ​ካማ ዛይሴ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ እንዲሁም ሌሎች ትምህርት ቤቶች ይገኙበታል።

​ይህ ሁኔታ የሺዎችን መሠረታዊ የመማር መብት የነፈገ ሲሆን፣ ተማሪዎች ጊዜያቸውን በከንቱ እያባከኑ ለቤተሰቦቻቸው ሸክም እንዲሆኑ ተገደዋል።
​
​እንደ ነዋሪዎቹና የአካባቢው ተወላጆች ገለጻ፣ ይህ ድርጊት ተራ የፀጥታ ችግር ሳይሆን በጋሞ ዞንና በክልሉ አመራሮች “የመዋቅር ጥያቄን ለማዳፈን” ታቅዶ እየተፈጸመ ያለ የዘር ማጥፋት ዘመቻ አካል ነው።

WT Media ቀደም ሲል ባደረጋቸው ተከታታይ ዘገባዎች እንዳረጋገጠው ​በርካታ ንጹሐን ዜጎች በመደበኛና ኢ-መደበኛ የፀጥታ ኃይሎች ጥቃት ተገድለዋል፤ ​ሴቶች ተደፍረዋል፣ ቤቶችና ንብረቶች በእሳት ጋይተዋል።

​የአካባቢው ዋነኛ የገቢ ምንጭ የሆነው የሙዝ ምርት ወደ ገበያ እንዳይወጣ በመከልከሉ እንዲበላሽ ተደርጓል፤ ይህም ኅብረተሰቡን ለከፋ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ዳርጎታል።
​
​ይህ ሁሉ ሰቆቃ በሕዝብ ላይ እየደረሰ ባለበት ወቅት፣ የክልሉና የዞኑ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ዝምታን መምረጣቸው በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ቁጭትን ፈጥሯል።

WT Media ጉዳዩን በሚመለከት ከዞንና ከክልል ባለሥልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት እስካሁን አልተሳካም።

​የዘይሴ ብሔረሰብ ጥያቄ ሕገ-መንግሥታዊ ምላሽ ማግኘት ሲገባው፣ በትምህርት ተቋማትና በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ለክልሉ ሰላም ጠንቅ እንደሆነ በጉዳዩ የተጠየቁት አንድ የሐዋሳ ዩንቨርስቲ ምሁር ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቶችን ለጦር ካምፕነት መጠቀም በዓለም አቀፍ ሕግም ሆነ በአገር ውስጥ ሕግ የተከለከለ ቢሆንም፣ በዘይሴ ግን ይህ ድርጊት በግልጽ እየተፈጸመ ይገኛል ይሄ አሳፋሪ ድርጊት እንደሆነ አብራርተዋል።

​የፌዴራል መንግሥትና የሚመለከታቸው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በዘይሴ አካባቢ እየደረሰ ያለውን ግፍ በአስቸኳይ እንዲመለከቱና ዝግ የሆኑ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ተማሪዎች ወደ ገበታቸው እንዲመለሱና ለህዝቡ ጥያቄ ዘላቂ ምላሽ እንዲሰጥ ማድረግ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት እንደሆነም ምሁሩ ጠቁመዋል።
​
​🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media