በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በአርባምንጭ ከተማና በጋሞ ዞን የተለያዩ መዋቅሮች ውስጥ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ንቁ ተሳትፎ ያላቸው ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር የማዋል ሰፊ ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን WT Media ካሰባሰባቸው የስፍራው መረጃዎች ለማወቅ ችሏል።
እስካሁን ባለው ሂደት ቢያንስ ከ20 በላይ ግለሰቦች መታሰራቸው ተረጋግጧል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በማኅበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴው የሚታወቀው ኩኔ ደመላሽ የተባለ ግለሰብ በፌዴራል ደኅንነት መሥሪያ ቤት መርማሪዎች በአርባምንጭ ከተማ በቁጥጥር ስር ውሎ ነበር።
ግለሰቡ የተጠረጠረበት “የፋኖ ታጣቂዎች ተልዕኮ በማስፈጸም፣ በማደራጀት፣ ድጋፍ በመሰብሰብ፣ አገራዊ ምርጫን ለማደናቀፍ በመንቀሳቀስና ስልታዊ ፕሮፓጋንዳ በመስራት” የሚል እንደሆነ ታውቋል።
ኩኔ በአርባምንጭ ፖሊስ ጣቢያ ለአንድ ሳምንት ታስሮ ከተፈታ በኋላ፣ በሁለተኛው ቀን በድጋሚ ተይዞ ወደ ጊዶሌ ማረሚያ ቤት ተወስዷል።
ይህ ግለሰብ ከመታሰሩ ከቀናት በፊት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ላይ የሚነሱትን “የሌብነት፣ የብልሹ አሠራር፣ የኢፍትሐዊነትና የሰብአዊ መብት ጥሰት” አጋልጠሃል በሚል የ WT Media መሥራችና ዋና አዘጋጅ Natnael Gecho Betalo ን ለመወንጀልና ሚዲያውን ( WT Media Facebook page) በዘመቻ መልክ ለማዘጋት በራሱ ገጽና በሌሎች አውታሮች ለሕዝብ ጥሪ ሲያቀርብ የነበረ መሆኑ ጉዳዩን ውስብስብ ያደርገዋል።
ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የክልሉን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተል ምሁር ለ WT Media እንደገለጹት፣ ይህ እርምጃ ከቀላል የወንጀል ጥርጣሬ በላይ የሰፋ የፖለቲካ መተናኮስ ውጤት ነው።
”የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የጥቅም ተጋሪዎችና ደጋፊዎች አብዛኞቹ ፀረ-ፌዴራል መንግሥት ናቸው” ያሉት ምሁሩ፤ ርዕሰ መስተዳድሩን ለመከላከልና ለማሞገስ ከፍተኛ ገንዘብ ተመድቦላቸው የተደራጁት የማኅበራዊ ሚዲያ ቡድኖች፣ በተመሳሳይ ሰዓት የፌዴራል መንግሥትን ለመቃወም፣ ተቀባይነት ለማሳጣትና ዐመፅ ለመቀስቀስ እየተጠቀሙባቸው እንደሆነ ታዝቤያለሁ ብለዋል።
አክለውም “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን በእጅ አዙር እየመራ የሚገኘው አርባምንጭና አካባቢውን መኖሪያ ያደረገው የፋኖ መዋቅር ነው። ለዚህም የተደራጀ የማኅበራዊ ሚዲያ፣ የስንቅና የሞራል ድጋፍ በክልሉ ባለሥልጣናት አጋዥነት እየተሰጠ ይገኛል” ሲሉ የፌዴራል ደኅንነት መሥሪያ ቤት የወሰደው እርምጃ እንዲያውም የዘገየ መሆኑን ጠቁመዋል።
በክልሉ ውስጥ ሆን ተብሎ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣና እንዲማረር የተጠና ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ምሁሩ ለዚህም ማሳያዎችን ”በዘይሴ አካባቢ የዘር ጭፍጨፋ ዘመቻ እንዲቀጥል መደረጉ፣ የቁጫ ሕዝብ በማንነቱ እንዲበደል መፈረዱ፣ በኮንሶ፣ በኮሬ፣ በቡርጂ፣ በጋርዱላ እና ሌሎች አካባቢዎች መሠረታዊ ልማት ሆን ተብሎ በመከልከል ከተጠቃሚነት ማግለላቸው፣ በዎላይታ፣ በጎፋ እና በጌዴኦ ሕዝቦች መካከል እርስ በርስ ክፍፍል በመፍጠር መንግሥታዊ ሌብነትን ማስፋፋታቸው” ጠቁመዋል።
“ይህንን አፍራሽ ተግባር ስኬታማ ለማድረግ ከክልሉ ባሻገር በሌሎች ክልሎችና በፌዴራል ደረጃ የሚገኙ አመራሮችም ጭምር የዓላማው ደጋፊና ተሳታፊ በመሆን በነፃነት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ” ተገልጿል።
በመጨረሻም ምሁሩ “ማንኛውም ሰላማዊ ሰው በሕገወጥ መንገድ መታሰር የለበትም። ነገር ግን ሕግ ጥሰው የተገኙ አካላት ካሉ ሰብአዊ ክብራቸው ተጠብቆ፣ በሕጋዊ ሥርዓት ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው ሊታይ ይገባል” ብለዋል።
እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ የጋሞ ዞንም ሆነ የክልሉ ኮሙኒኬሽን የሰጠው ምንም ዓይነት መግለጫ የለም። WT Media ከተለያዩ ባለሥልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። ቢሆንም የጉዳዩን ሂደት በቅርበት ተከታትሎ የሚያቀርብ ይሆናል።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media