በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በአርባ ምንጭ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ የሚገኙትና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፍትሕ ውሳኔ የሰጣቸው ወጣት ባለሀብት እንጂነር ብርሃነመስቀል ክንፌ (የማራ ማይነርስ ዋና ሥራ አስኪያጅ)፤ በጽኑ ታመው በሕክምና ላይ እያሉና ራሳቸውን ስተው በወደቁበት ሁኔታ፣ በትናንትናው ዕለት በጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በግዳጅ ችሎት እንዲቀረቡ መደረጉን ባለቤታቸው ለWT Media በምሬትና በከፍተኛ ሐዘን ገልጸዋል።
WT Media ይሄንን ጉዳይና ከጀርባው ያለውን የአስተዳደር በደል በተደጋጋሚ የሚዲያ ሽፋን በመስጠት በቅርበት ሲዘግብ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፤ በትናንትናው ዕለት በጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተፈጸመው ድርጊት ግን ፍፁም ፍትሕ የጎደለውና ሰብአዊ መብትን የጣሰ የበቀል እርምጃ ነው ሲሉ ባለቤታቸው ይከሳሉ።
የባለሀብቱ ባለቤት ለሚዲያችን እንደገለጹት፣ ብርሃነመስቀል ካለባቸው የጤና እክል ጋር ተያይዞ በሆስፒታል በሕክምና ዕርዳታ ላይ የነበሩ ቢሆንም፣ ከሕክምና (Stretcher) ላይ በፖሊስ ጥበቃ ተገድደው ወደ ፍርድ ቤት እንዲመጡ ተደርጓል።
ባለቤታቸው የችሎቱን አስከፊ ሁኔታ በዕንባ ሆነው እንዲህ ሲሉ ለWT Media አጋርተዋል።
”ባለቤቴ መቆም እንኳ በማይችልበት፣ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀጠቀጠ ባለበት ሁኔታ ነው ደግፈው ችሎት ያቀረቡት። ፍርድ ቤት ውስጥ ራሱን ስቶ ሲወድቅ እንኳ በሰብአዊነት እንዲነሳ ፈቃደኛ አልነበሩም…” ብሏል።
ባለፈው አርብ ዕለት ፍርድ ቤቱ ብርሃነመስቀልን “ተሰብሮ ይታይ አይታይ” የሚለውን የዕግድ መዝገብ አስመልክቶ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ ትናንት ሰኞ ዕለት ግን ችሎቱ መዝገቡን ባልተለመደ አሠራር ወደ ሌላ ጉዳይ በመቀየር ተከሳሹ የዕምነት ክህደት ቃል እንዲሰጡ መጠየቁን ባለቤታቸው ያስረዳሉ።
ብርሃነመስቀል ክንፌ በበኩላቸው፣ ጠበቃቸው ባልተገኘበት፣ በጽኑ ታመውና መናገር እንኳ በማይችሉበት የጤና ሁኔታ ላይ ሆነው የቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ ከባድ በመሆኑ፣ ተዘጋጅተው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠት እንደማይችሉ ለችሎቱ ለማስረዳት ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
ጉዳዩን በጽሑፍ ጭምር ለችሎቱ ለማቅረብ ያደረጉት ጥረትም በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደርጎባቸዋል።
ይባስ ብሎም፣ ተከሳሹ በበሽታ ምክንያት መናገር አለመቻላቸውንና ፈቃደኛ አለመሆናቸውን እንደ መቃወም በመቁጠር፣ የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለፊታችን ሰኔ 11 ቀን 2018 ዓ.ም የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች እንዲሰሙ ብይን ማሳለፉ ታውቋል።
ይህ የችሎቱ ፍፁም ሰብአዊነት የጎደለውና ሕገ-መንግሥታዊ የመከላከያ መብትን የገፈፈ አካሄድ፣ እዚያ በነበሩት ታዛቢዎችና ራሳቸውን እንጂነር ብርሃነመስቀልን በታጠቁ ፖሊሶች አስገዳጅነት ደግፈው ባመጡት በማረሚያ ቤቱ ሠራተኞች ዘንድ ጭምር ከፍተኛ ድንጋጤንና ማዘንን መፍጠሩ ተገልጿል።
የባለሀብቱ ባለቤት ለአዝማሚያው ማብራሪያ ሲሰጡ፤ ከዚህ ቀደም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰጠውና ባለሀብቱንና ድርጅታቸውን (ማራ ማይነርስ) ነፃ ያደረገው፥ የክልሉን ማዕድን ባለሥልጣን በገንዘብ የቀጣው የዕግድ ውሳኔ በተዋረድ መሬት ላይ መተግበር የነበረበት ቢሆንም፣ አሁን በጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በግልጽ እየተሄደበት ያለው ሒደት ግን ፍትሕን የማጓተትና ባለሀብቱን በአካል የማጥፋት ስውር ዓላማ ያለው ይመስላል ብለዋል።
WT Media የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ የፌዴራል ፍትሕ ሚኒስቴር እና የሚመለከታቸው የሕግ የበላይነት ተሟጋቾች በአርባ ምንጭ ማረሚያ ቤትና በጋሞ ዞን ፍርድ ቤት በባለሀብቱ ብርሃነመስቀል ላይ እየተፈጸመ ያለውን ይሄንን አስከፊ ግፍ በአስቸኳይ እንዲመረምሩና የባለሀብቱን ሕይወት እንዲታደጉ በጥብቅ ይጠይቃል።