በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሥር በሰደደው የአስተዳደር በደልና መዋቅራዊ የፍትሕ እጦት ሳቢያ፣ ንብረቱ ተቀምቶ በአሁኑ ሰዓት በአርባምንጭ ማረሚያ ቤት ታስሮ የሚገኘው ወጣት ባለሀብት እንጂነር ብርሃነ መስቀል ክንፈ (የማራ ማይነርስ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ) ጉዳይን በተመለከተ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትናንት ግንቦት 11 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው ችሎት በክልሉ ባለሥልጣናት ላይ ጠንካራ የወንጀል ምርመራና የቅጣት ማዘዣዎችን የያዘ አስገዳጅ ታሪካዊ ውሳኔ አስተላልፏል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሥር በሰደደው የአስተዳደር በደልና መዋቅራዊ የፍትሕ እጦት ሳቢያ፣ ንብረቱ ተቀምቶ በአሁኑ ሰዓት በአርባምንጭ ማረሚያ ቤት ታስሮ የሚገኘው ወጣት ባለሀብት ብርሃነመስቀል ጉዳይን በተመለከተ፣ WT Media ይሄንን ጉዳይና ከጀርባው ያለውን የአስተዳደር በደል በተደጋጋሚ የሚዲያ ሽፋን በመስጠት በቅርበት ሲዘግብ መቆየቱ ይታወቃል።
ይህንን ተከትሎ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትናንት ግንቦት 11 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው ችሎት በክልሉ ባለሥልጣናት ላይ ጠንካራ የወንጀል ምርመራና የቅጣት ማዘዣዎችን የያዘ አስገዳጅ ታሪካዊ ውሳኔ አስተላልፏል።
WT Media ከችሎት ምንጮች በቀጥታ ባገኘው ይፋዊ ሰነድና የችሎት ውሳኔ መግለጫ መሠረት፣ ፍርድ ቤቱ በመዝገብ ቁጥር 330360 የክልሉን ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ (የማዕድን ባለሥልጣንን) ሕገወጥ አካሄድ ሙሉ በሙሉ ያጋለጠ አምስት ውሳኔ ሰጥቷል።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀደም ሲል የሰጠውን ሕጋዊ የዕግድ ትዕዛዝ ወደ ጎን በመተውና ፍርድ ቤትን በመናቅ፣ የክልሉ ውሃ፣ ማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮ (የማዕድን ባለሥልጣን) የፈጸመውን ሕገወጥ ተግባር መርምሮ በገንዘብ እንዲቀጣ ወስኗል።

የፍርድ ቤቱን ይፋዊ የዕግድ ትዕዛዝ በመተላለፍና ሥልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም የወንጀል ድርጊት በፈጸሙ የመንግሥት አካላትና ባለሥልጣናት ላይ የፌዴራል ፖሊስ በአስቸኳይ የወንጀል ምርመራ እንዲያካሂድና ለሕግ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ በጥብቅ አዟል።
በፍርድ ቤት የታገደውን ቦታ በመውረርና ዕግድ በመጣስ ማዕድኑን ሲያመርቱ የነበሩ ሕገወጥ ድርጅቶችና ግለሰቦች በአስቸኳይ ከቦታው እንዲወጡ የተወሰነ ሲሆን፤ የክልሉ ፖሊስና የቦረዳ ወረዳ ፖሊስ ቦታው ላይ በጥብቅ ጥበቃ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
የክልሉ ቢሮ “የአስተዳደር ውል በግልግል ዳኝነት ሊታይ አይችልም” በማለት ያቀረበውን መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ውድቅ በማድረግ፣ በማዕድን ሥራዎች አዋጅ ቁጥር 678/2002 አንቀጽ 76 መሠረት ክርክሩ በገለልተኛ የግልግል ዳኞች ጉባኤ (Arbitration) እንዲታይ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ አጽንቶታል።
የፍርድ ቤቱን ዕግድ በመጣስ ወንጀል የፈጸሙ አካላት በ”ማራ ማይነርስ” ድርጅት ላይ ላደረሱት ከፍተኛ የኢኮኖሚና የንብረት ጉዳት፣ ባለሀብቱ በፍፍትሐብሔር ክስ ተገቢውን ካሳ እንዲያገኝ መብቱ ተጠብቆ መዝገቡ ተዘግቷል።
ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉ የሕግ ባለሙያዎች ለ WT Media እንደገለጹት፤ ይህ ውሳኔ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሕግን ጥሰው ባለሀብቶችን ማሰርና ንብረት መውረስ እንደማይችሉ ያሳየ ትልቅ የፍትሕ ድል ነው።
”የክልሉ ማዕድን ቢሮ ልዩ አዋጁን (አዋጅ ቁጥር 678/2002) ጥሶ ክርክሩን ለዓመታት ማጓተቱና ባለሀብቱ ፍርድ ቤት ላይ በሕግ እያሸነፈ ባለበት አውድ ውስጥ በአካል በአርባምንጭ ማረሚያ ቤት እንዲታሰር መደረጉ፣ በክልሉ ውስጥ ሕግ አስከባሪ ተቋማት የባለሥልጣናትን ድብቅ ፍላጎትና የግል ጥቅም ማስፈጸሚያ መሣሪያ መሆናቸውን በግልጽ ያሳያል” ብለዋል።
ባለሀብቱ እንጂነር ብርሃነ መስቀል ክንፈ በማረሚያ ቤት ሆኖ ያደረገው የተደራጀ የፍትሕ ትግል በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ደረጃ አሸናፊ ሆኖ ወጥቷል። ውሳኔው የዕግድ ትዕዛዝ መጣስ በመንግሥት መዋቅር ውስጥም ቢሆን የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚያስከትል ማረጋገጫ ሰጥቷል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፍትሕ ቢሮ፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የክልሉ ፖሊስ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በትናንትናው ዕለት የሰጠውን ይህንን አስገዳጅ ትዕዛዝ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲያደርጉ፣ ሕገወጦችን ከማዕድን ቦታው እንዲያስወጡና በሙስና የተዘፈቁ ባለሥልጣናትን ለሕግ እንዲያቀርቡ WT Media ይጠይቃል። ጉዳዩን እስከ ፍጻሜው በቅርበት መከታተላችንን እንቀጥላለን!