በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን መዋቅር ሥር የሚገኙት የዘይሴ እና የቁጫ ብሔረሰቦች፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ለማስከበር ከሚያደርጉት የህልውና ትግል ባሻገር በመጪው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ የሚያስችላቸው መሰረታዊ መብት ጭምር በአሁኑ ወቅት እጅግ አሳሳቢና አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱን የሁለቱ ብሔረሰቦች ተወካዮችና የፖለቲካ አመራሮች ለ WT Media ገልጸዋል።
በአካባቢው ላይ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ ቀርቶ ዕጩ ተወዳዳሪዎችም ሆኑ መራጮች የምርጫ ካርድ እንዳይወስዱ በገዥው ፓርቲ መዋቅሮችና በጸጥታ ኃይሎች መከልከላቸውና ጫና እየተደረገባቸው መሆኑ ተገልጿል።
በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሊካሄድ ከታቀደው 7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ በአካባቢው በሰፈኑት የጸጥታ ኃይሎችና በገዥው ብልጽግና ፓርቲ ካድሬዎች አማካኝነት እየተፈጸመ ያለው የጅምላ እስራት፣ ግድያ፣ የፓርቲ ጽሕፈት ቤቶች መታሸግ እና የምርጫ ቅስቀሳ ዕገዳ ቀውሱን ወደ ከፋ ደረጃ አሸጋግሮታል። WT Media በወቅታዊ ዝርዝር ጉዳዮችን በተመለከተ ከሁለቱም ብሔረሰቦች ተወካዮች ጋር በዛሬው ዕለት ጥልቅ ቃለ-መጠይቅ አድርጓል።
በዚህም የዘይሴ ልዩ ምርጫ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) አባል የሆኑትና በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ዕጩ ሆነው የቀረቡት አቶ አብራሃም አሞሼ ለአካባቢያቸው ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪና አስከፊ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ አቶ አብራሃም ማብራሪያ ከሆነ፣ የክልሉ አድማ ብተና ፖሊስ አባላት በአካባቢው በሚገኙ ቁልፍ የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ውስጥ የራሳቸውን ካምፕ በመሥራትና ምሽግ በመቆፈር ሰፍረው ይገኛሉ። ፖሊሶቹ የመሸጉባቸው ተቋማት መካከል፦
- የሕዝብ ጤና ጣቢያዎች
- የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች
- የማዘጋጃ ቤት ሕንጻዎች እና የቀበሌ ጽሕፈት ቤቶች ይገኙበታል።
ይህ እርምጃ የሕዝቡን የዕለት ተዕለት ሕይወት ያደናቀፈ ሲሆን የጋሞ ዞን መደበኛ ፖሊሶችም በየቀኑ ምሽት ሕዝቡን በማሳደድ፣ በመግደል፣ ከየቤቱ በማሰር፣ ንብረትና ገንዘብ በመዝረፍ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት የዘይሴን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆ ከፍተኛ ጫና እያሳደረበት መሆኑን የጠቀሱት አቶ አብራሃም፤ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እና የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ደሚሴን ጨምሮ ሌሎች የጋሞ ብሔረሰብ ተወላጆች የዘይሴን ብሔረሰብ ሙሉ በሙሉ ወደ ጋሞ ብሔረሰብ ማንነት የመቀየርና መልካዓ-ምድሩንም ጭምር በመውረስ “የጋሞ ምድር” የማድረግ አጀንዳ ይዘው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ሳቢያ ቀጥተኛ የማንነት፣ የባህል፣ የታሪክና የጭቆና ወረራ እየተካሄደ ሲሆን፣ እስካሁን ባለው ሂደት ብቻ ከ100 በላይ ሰዎች የተገደሉበት፣ በሰሞኑ እንቅስቃሴ ደግሞ ከ192 በላይ ሰዎች ያለ ምንም ወንጀላቸው በግፍ የታሰሩበትና የተሳደዱበት ሁኔታ መኖሩን ተወካዩ ይፋ አድርገዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በጋሞ ዞን መዋቅር ሥር የሚገኘው የቁጫ ብሔረሰብም የከፋ መዋቅራዊ እና ሰብአዊ መብት ጥሰት ሰለባ ሆኗል።
የቁጫ ብሔረሰብ የራሱ የሆነ የዳበረ ቋንቋ፣ ባህል፣ ልዩ እሴትና ታሪክ ያለው ቢሆንም፣ የብሔር ማንነቱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ገና ዕውቅና ያላገኘ በመሆኑ ለማንነቱ ዕውቅና፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትና የራሱ መዋቅር ተከልክሎ በጋሞ ዞን ከፍተኛ በደል እየደረሰበት ይገኛል።
የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) በ2013 ዓ.ም. በነበረው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በቁጫ ምርጫ ክልል ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ አግኝቶ ማሸነፉ ይታወሳል። ይሁን እንጂ ካሸነፈበት ማግስት ጀምሮ እስካሁን የምርጫ ዋዜማ ድረስ ገዥው ብልጽግና ፓርቲ በመዋቅሩ እና በፀጥታ ኃይሎቹ አማካኝነት ከ16 በላይ የፓርቲውን ፅህፈት ቤቶች በኃይል አሽጓል።
የቁጫ ብሔረሰብ አባል፣ የክልል ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ እና የፓርቲው ፅህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ባንድራ በላቸው ለWT Media እንደገለጹት፣ የብሔረሰቡን መብት ለማስከበር የሚንቀሳቀሱ አባላትና አመራሮች ላይ ከባድ ወታደራዊና ፖለቲካዊ እንግልቶች፣ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚፈጸሙ እስራቶች እና የግድያ ሙከራዎች እየተፈጸሙ ይገኛሉ።

ሁለቱም ብሔረሰቦች በመጪው ምርጫ ተሳትፈው የፖለቲካ ውክልና ለማግኘት ቢዘጋጁም፣ በገዢው ፓርቲ (ብልጽግና) እና በአካባቢው የጸጥታ መዋቅሮች በኩል የሚደረገው ሕገ-ወጥ ጫና የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሂደቱን ሙሉ በሙሉ አደጋ ላይ ጥሎታል።
የኢዜማ ዕጩ አቶ አብራሃም አሞሼ በአካባቢው ገብተው ማኒፌስቶአቸውን ለመግለጽና የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ በፍጹም እንዳልቻሉ ገልጸዋል። የገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና የጸጥታ ኃይሎች የኢዜማ ዕጩዎችን ሙሉ በሙሉ እያሳደዱና እያስፈራሩ ይገኛሉ።
ይህ እውነታ ምርጫው ፍትሐዊና ነፃ የመሆኑን ተስፋ ጨለማ ቢያደርገውም፣ የዘይሴ ሕዝብ ግን ከዚህ ቀደም በተደረጉ ቅስቀሳዎችና ሕዝቡን ከጭቆና ነፃ ለማውጣት በተያዘው የፓርቲው ዓላማ ማኒፌስቶውን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ፣ መብቱን ለማስከበር በነቂስ ወጥቶ ለመምረጥ የሚያገለግል ካርድ መውሰዱን አቶ አብራሃም አረጋግጠዋል።
በቁጫ ምርጫ ክልልም የቁሕዴፓ አባላትና አመራሮች በምርጫ ክልሉ ገብተው እንዳይቀሰቅሱ፣ የፓርቲውን ዓርማ፣ ባንዲራ እና ምልክት ይዘው የአደባባይ ቅስቀሳ እንዳያደርጉ በሕገ-ወጥ መንገድ የታገዱ ሲሆን ከመንገድ መመለስ፣ መባረር እና የግድያ ዛቻዎች ተሰንዝረውባቸዋል።
የምርጫ ካርድ የወሰዱ ዜጎች ቁሕዴፓን እንዳይመርጡ በአደባባይ ከፍተኛ ማስፈራራት እየደረሰባቸው ሲሆን፣ ገዥው ፓርቲ የመራጮችን ካርድ ወደኋላ መልሶ በመሰብሰብ መታወቂያቸውን እየመዘገበ፣ ሕዝቡን መደብደብ፣ በገንዘብ መቅጣት እና የጥላቻ ስድብ የመሰንዘር ድርጊቶችን በስፋት እየፈጸመ ይገኛል።
በተጨማሪም ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላቶቻቸው በነፃነት መንቀሳቀስ እንዳይችሉ ተደርገዋል። በአንጻሩ ገዥው የብልጽግና ፓርቲ የራሱን አባላት በማህበራዊ መሠረት የሌላቸው የሌሎች ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ስም ዕጩ አድርጎ በማቅረብ “የጋራ ምክር ቤት” በሚል የይስሙላ የጋራ መድረክ ፈጥሯል። እነዚህ ፓርቲዎች በምርጫ ወረቀት ላይ ቢታተሙም፣ በተግባር ግን የብልጽግናን የምርጫ ቅስቀሳ የሚያግዙ መሆናቸውን አቶ ባንድራ አጋልጠዋል።
የዘይሴ ብሔረሰብ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ሲጸድቅ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ከተመዘገቡትና የምክር ቤቱ መሥራች ከሆኑት ብሔረሰቦች መካከል አንዱ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ የራሱ የሆነ ራሱን የቻለ አስተዳደራዊ መዋቅር (ልዩ ወረዳ) አልተሰጠውም። ሕዝቡ ይህንን ጥያቄ ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ በተከታታይ ሲጠይቅ ቆይቷል።
የመዋቅር ጥያቄው ታሪካዊ ሂደትና የተፈጸመው አድልዎ፦
- የ2010 ዓ.ም. ዳግም መነሳሳት፦ በአገሪቱ የመጣውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ፣ የዘይሴ ሕዝብ ቀድሞ ሲጠይቅ የነበረው የመዋቅር ጥያቄ ሕጋዊ ምላሽ እንዲያገኝ ጥያቄውን በይፋ አድበስብሰ።
- የ2011 ዓ.ም. የጋራ ጥናት፦ በወቅቱ በነበረው የደቡብ ክልል መንግሥት ውሳኔ መሠረት፣ የዘይሴ የልዩ ወረዳ መዋቅር ጥናት ከማሬቆ፣ መስቃን፣ ቀበና እና ጣንባሮ ብሔረሰቦች ጋር በአንድ ላይ ተጠናቀቀ።
- መዋቅራዊ አድልዎ፦ በአንድ ላይ የተጠኑትና በአሁኑ ወቅት ወደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተመደቡት ማሬቆ፣ መስካን፣ ቀበና እና ጣንባሮ የልዩ ወረዳ መዋቅር ሲሰጣቸው ዘይሴ ግን ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እንዲካተት ተደረገ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ የዘይሴን የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ ሆን ብለው በማፈናቸውና ውሳኔውን በመከልከላቸው ጥያቄው እስካሁን ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል። የኢፌዲሪ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአካባቢው ያለውን ውጥረትና አቤቱታ መሠረት በማድረግ ወደ 11 ዙር የሚጠጉ ጉዞዎችን ወደ ዘይሴ ምድር በማድረግ ሰፊ ማጣራት ቢያደርግም፣ በ11ዱም ዙር ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው የዘይሴ ሕዝብ ሳይሆን የአካባቢው ገዢ መንግሥት፣ የብልጽግና ፓርቲ አመራርና የዞኑ የጸጥታ መዋቅር መሆናቸውን አቶ አብራሃም አሞሼ አስታውሰዋል።
የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) በአካባቢው የደረሱትን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች፣ የፖሊስ ድብደባዎችን እና ተያያዥ የቪዲዮ፣ የፎቶ እና የድምፅ ማስረጃዎችን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተደጋጋሚ ቢያቀርብም፣ ቦርዱ ጥፋት የፈጸመውን የብልጽግና ፓርቲን ከምርጫ ክልሉ ከማገድ ይልቅ “የመንደር ሽማግሌ የመሸማገል ዓይነት” አካሄድ ሲከተል መቆየቱን አቶ ባንድራ ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሳይቀር ወደ ምርጫ ክልሉ በመሄድ በሕዝቡ ላይ ጥላቻ ያዘለ ንግግር ማድረጉን የገለጹት አቶ ባንድራ፣ ይህንን የጥላቻ ንግግር በቪዲዮና በድምፅ ጭምር ለምርጫ ቦርድ አቅርበው ፈጣን ምላሽ ባለማግኘታቸው፣ ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ.ም ጉዳዩን ወደ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመውሰድ ምርጫው እንዲታገድ ክስ መመስረታቸውንና ለምርጫ ቦርድም መጥሪያ ማድረሳቸውን አረጋግጠዋል።

የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሊካሄድ የታሰበው ምርጫ የዜጎችን ሕገ-መንግሥታዊ መብት ፍጹም የሚጋፋ በመሆኑ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ ግንቦት 19 ቀን 2018 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ አውጥቷል፦
- በቁጫ ምርጫ ክልል የሚደረገውን ለአንድ ወገን ያደላ አግላይ ምርጫ እና የምርጫ ውጤቱን ሙሉ በሙሉ አይቀበልም።
- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የፌዴራል መንግሥት እና የሰብዓዊ መብት ተቋማት አስቸኳይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ ይጠይቃል።
- በቁጫ ምርጫ ክልል 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለጊዜው ታግዶ እንዲቆይ እና የተፈጸሙት ሕገ-ወጥ ግድፈቶች ታርመው ምርጫው ከሁለት ወር ባላነሰ እና ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንዲካሄድ ቦርዱ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ አበክሮ ይጠይቃል።
“ፍትሐዊ ምርጫ ለዴሞክራሲ ግንባታ!” በሚል መሪ ቃል ፓርቲው የቁጫ ሕዝብን መብት ለማስከበር የተለመደውን ፍፁም ሰላማዊ እና ሕጋዊ ትግል አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጧል።
በጋሞ ዞን ሥር የሚገኙት የዘይሴ እና የቁጫ ብሔረሰቦች እያካሄዱት ያለው ትግል የፓለቲካ ስልጣን ፍላጎት ሳይሆን የማንነት፣ የታሪክና የህልውና ጉዳይ መሆኑን የሁለቱ ብሔረሰቦች አመራሮች ያስረዳሉ።
በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት ለማካሄድ እንዲሁም የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ የሚከተሉት አስቸኳይ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባ ተወካዮቹ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፦
- በአካባቢው ሰፍረው የሚገኙትና ሕዝቡን እያሸበሩ ያሉት የክልሉ አድማ ብተና ፖሊስ፣ የጋሞ ዞን መደበኛ ፖሊስና የሚሊሻ ኃይሎች በአስቸኳይ አካባቢውን ለቀው መውጣት አለባቸው።
- የአካባቢውን የጸጥታ ክፍተት ለመሙላትና ፍጹም ገለልተኛ የሆነ ሰላም ለማስፈን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ወይም የፌደራል ፖሊስ አባላት በአስቸኳይ ሊሰማሩ ይገባል።
- የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዘይሴን የልዩ ወረዳ መዋቅር ጥያቄ እንዲሁም የቁጫን የማንነት ዕውቅና ጥያቄ ሕገ-መንግሥታዊ በሆነ መንገድ በአስቸኳይ ምላሽ መስጠት አለባቸው።
ይህ ካልሆነ ግን በአካባቢው እየተባባሰ የመጣው ሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የጅምላ ግድያ እና የማንነት ማጥፋት ዘመቻ ወደማይመለስና መላውን ክልል ወደሚያናጋ ከባድ የእርስ በርስ ቀውስ ሊያመራ እንደሚችል ተወካዮቹ ስጋታቸውን በጽኑ ገልጸዋል።
WT Media በተደጋጋሚ እንደዘገበው፣ የዘይሴ ብሔረሰብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በጋሞ ዞን መዋቅር ውስጥ የሚገኝ እና የብሔር ማንነቱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ዕውቅና ያገኘ፣ የራሱ ልዩ እሴት ያለው ሕዝብ ነው። ሆኖም ግን፣ ለብሔረሰቡ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እና የራሱ መዋቅር ተከልክለው በጋሞ ዞን የዘር ማፅዳት ዘመቻ እየተካሄደበት ይገኛል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ቁጫ ብሔረሰብ በተመሳሳይ ሁኔታ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በጋሞ ዞን መዋቅር ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም፣ የብሔር ማንነቱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ዕውቅና ገና ያላገኘ የራሱ ልዩ እሴት ያለው ሕዝብ ነው። ይህ ብሔረሰብ ለማንነቱ ዕውቅና መከልከሉ ሳያንስ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እና የራሱ መዋቅር ተከልክለው በጋሞ ዞን ከፍተኛ በደል እየደረሰበት ይገኛል።
በጉዳዩ ዙሪያ አጭር ሀሳብ እንዲሰጡበት በWT Media የተጠየቁት የአዲስአበባ ዩንቨርስቲ ፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ዶክተር ስጦታው አረጋ “በጋሞ ዞን ሥር በሚገኙት በእነዚህ ሁለት ብሔረሰቦች ላይ እየተፈጸመ ያለው ሁለንተናዊ መዋቅራዊ ጫና፣ የአካባቢው የምርጫ ሂደት ከዴሞክራሲያዊ መርሆዎች ሙሉ በሙሉ ያወጣውና የሕዝቡን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ መሆኑን ያሳያል። ነፃና ገለልተኛ የሆኑ የፌደራል የጸጥታ አካላት በአካባቢው ሳይሰማሩ፣ እንዲሁም ሕገ-መንግሥታዊ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄዎች ሕጋዊ ምላሽ ሳያገኙ የሚካሄድ ምርጫ ቀውሱን ከማባባስ ባለፈ ዘላቂ ሰላምን ሊያመጣ እንደማይችል ግልጽ ሆኗል” የሚል ጠንካራ አስተያየት ሰጥተዋል።
WT Media በዚህ ዘገባ ላይ ከተነሱት ከባድ የወንጀልና የአፈና ክሶች እንዲሁም በብሔረሰቦቹ ላይ እየደረሱ ስላሉት በደሎች በተመለከተ፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን የአካባቢውን ባለሥልጣናት፣ የጋሞ ዞን አስተዳደርን እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ምላሽና አስተያየት ለማካተት በተደጋጋሚ ተንቀሳቅሷል። ሆኖም ግን ከሚመለከታቸው አካላት በኩል ስልኮችን ባለማንሳትና ፈቃደኛ አለመሆን የተነሳ ምላሻቸውን ለማግኘት የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።