በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ላይ የሚገኘው ታሪካዊው ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመጣው የይገባኛል ጥያቄ፣ የህገ-ወጥ ሰፋሪዎች መስፋፋት እና በታጣቂዎች የፀጥታ ስጋት ምክንያት ህልውናው አደጋ ላይ መውደቁ ይነገራል።
ሰሞኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እና የጋሞ ዞን ከፍተኛ አመራሮች በፓርኩ ውስጥ ያደረጉት ጉብኝትና ተያይዘው የወጡ መረጃዎች ደግሞ የፓርኩን ውስብስብ ችግሮች ይበልጥ አግጠው አውጥተዋል።
ለ WT Media ከውስጥ ምንጮች የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እና የጋሞ ዞን አመራሮች በነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ወደ መሀል ገብተው ለመጎብኘትና ፎቶ ለመነሳት ሲንቀሳቀሱ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ጋር ተኩስ ተከፍቷል።
በዚህም ምክንያት የልዑካን ቡድኑ ወደ መሀል ፓርኩ መጓዝ ሳይችል ቀርቶ ከተወሰነ ቦታ ላይ ጥቂት ፎቶዎችን ብቻ በመነሳት በፍጥነት ለመመለስ ተገድዷል።

የመረጃ ምንጮች እንደሚሉት፤ ርዕሰ መስተዳድሩ በፓርኩ ላይ የተደቀነውን የህልውና እና የፀጥታ አደጋ ከሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል አካላት ጋር በዘላቂነት መፍታትን ትተው፣ አገራዊ ምርጫ መቃረቡን ተከትሎ የህዝቡን ቅሬታ ለማስታገስ ብቻ “ለማህበራዊ ሚዲያ ፍጆታ የሚሆን ፎቶ ተነስቶ ጥሎ ወጥቷል” ሲሉ ይተቻሉ።
ራሳቸው የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣን እንኳን ሳይቀሩ በከፍተኛ ጥበቃ ጭምር በፓርኩ ውስጥ መቆየት አለመቻላቸው በአካባቢው ያለውን የፀጥታ ስጋት ምን ያህል የከፋ መሆኑን ያሳያል።
ጉብኝቱን ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩ ምስሎች በክልሉ ውስጥ ሌላ የይገባኛል ውዝግብ ቀስቅሰዋል። ለምርጫ ቅስቀሳ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና የጋሞ ዞን አመራሮች በፓርኩ ውስጥ “Visit Gamo” የሚል ባነር ይዘው የተነሱትን ፎቶ ማጋራታቸውን ተከትሎ የኮሬ ዞን ከፍተኛ ቅሬታ አቅርቧል።

የኮሬ ዞን ወገኖች “ከግማሽ በላይ የፓርኩ ይዞታ የእኛ ሆኖ ሳለ የጋሞ ዞን ብቻ አድርጎ ማቅረብ አግላይና ታሪካዊ ይዞታችንን የሚክድ ነው” በማለት ተቃውሟቸውን እየገለጹ ይገኛል።
በነጭ ሳር ፓርክ እና በአባያ ሐይቅ ዙሪያ ያለው የፀጥታ መደፍረስ አዲስ እንዳልሆነ WT Media መዘገቡ ይታወሳል። ከሰባት ወራት በፊት ባለቤትነቱ የጋሞ ልማት ማኅበር የሆነችውና እስከ 30 ሰው የመያዝ አቅም ያላት “ባይራ” የተሰኘችው ዘመናዊ የቱሪስት መዝናኛ ጀልባ በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ታግታ እንደነበር ይታወሳል።
በወቅቱ በውስጧ የነበሩ ተሳፋሪዎች በከፍተኛ የገንዘብ ክፍያ የተለቀቁ ሲሆን፣ ጀልባዋ ግን ለቀናት ከቆየች በኋላ በ WT Media ይፋዊ ዘገባ እና በዞኑ አስተዳደር ከፍተኛ ምስጢራዊ ድርድር መለቀቋ ይታወሳል። ይህ ኩነት በአካባቢው የቱሪስት እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ጥላ ማጥላቱ አይዘነጋም።
በሌላ በኩል ፓርኩን በተመለከተ በኦሮሚያ ክልል እና በጋሞ ዞን መካከል ያለው የይገባኛል ጥያቄ ዓመታትን ያስቆጠረና አሁንም ያልተፈታ አጀንዳ ሆኖ በህብረተሰቡ ከፍተኛ ቅሬታ እያስነሳ የሚገኝ እንደሆነ በርካቶች ይገልፃሉ።
ለአብነት ከአንድ ዓመት በፊት የጋሞ ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ የነበሩት አቶ ታከለ ሀሚሶ ፓርኩ በ1966 ዓ.ም ከተመሰረተ ጀምሮ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ በጋሞ ይተዳደር እንደነበር ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ከኦሮሚያ ጉጂ አካባቢዎች የመጡ ከአንድ ሺሕ በላይ አባወራዎች በህገ-ወጥ መንገድ ከ25 ኪሎ ሜትር በላይ ወደ ውስጥ ዘልቀው በመስፈራቸው የፓርኩ 50 በመቶ ይዞታ መውደሙን መግለፃቸውን ዘግበን ነበር።
ሰፋሪዎቹ በፓርኩ ውስጥ የመንግስት መዋቅር ጭምር በመዘርጋት ጤና ተቋማትን፣ ትምህርት ቤቶችንና መኖሪያዎችን በመስራት፣ የደን ጭፍጨፋና የአደን ወንጀሎችን በመፈጸም ብርቅዬ እንስሳትን ለአደጋ እያጋለጡ መሆኑን ይናገራሉ። ህገ-ወጥ ሰፋሪዎችን ለማስነሳት ከኦሮሚያ ክልል ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ወደ ትግበራ አለመግባቱ ችግሩን አወሳስቦታል።
ይሁን እንጂ በወቅቱ የኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ጉጂ ዞን ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ዳዊት ዘለቀ ይህንን መረጃ ሙሉ በሙሉ በማስተባበል፤ “ነዋሪዎቹ የሚገኙት በነባር ይዞታቸው እና በራሳቸው ክልል ነው፤ ፓርኩም በኦሮሚያ ከሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች አንዱ ነው” የሚል ተቃራኒ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣንም ቢሆን በበኩሉ ህገ-ወጥ ሰፋሪዎችና አደን መኖሩን ቢያምንም፣ የባለቤትነት ጥያቄው ግን “በጥናት ያልተረጋገጠ ነው” በሚል በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ፍጥጫ ሳያበርድ ቆይቷል።
በአንድ በኩል የኦሮሚያ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የይገባኛል ፍጥጫ፥ በሌላ በኩል ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በጋሞ እና በኮሬ ዞኖች መካከል እየተቀጣጠለ ያለው አዲስ ቅሬታ፣ እንዲሁም በአካባቢው የተደቀነው የሸኔ ታጣቂዎች የፀጥታ ስጋት የሀገሪቱን ብርቅዬ የተፈጥሮ ሀብት ወደ ውድመት እየመራው ይገኛል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሰሞኑን ለምርጫ ቅስቀሳ ያደረጉትና በስጋት የተሞላው የ”ፎቶ ዘመቻ” ችግሩን ከማስታገስ ይልቅ፣ በዞኖች መካከል ያለውን መቃቃር ይበልጥ እንዳባባሰው የዘርፉ ታዛቢዎች ይገልጻሉ።
የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ህልውና እንዲጠበቅ ከተፈለገ ከፖለቲካዊ ፍጆታ በዘለለ የፌደራል መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት አስቸኳይና ዘላቂ መፍትሄ ሊፈልጉለት እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎቹ ይጠቁማሉ።