በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ሥር በሚገኝባቸው አሰኮ፣ ሺርካ እና ሆንቆሎ ዋቤ ወረዳዎች ውስጥ ግንቦት 23 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በተሰነዘረ የተቀናጀ ጥቃት የ13 ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ሕይወት ማለፉን የአንድ ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን መቃጠሉንና ሰፊ መፈናቀል መከሰቱን ሀገረ ስብከቱ አስታውቋል።
የአርሲና ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ለሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ መሠረት፣ በጥቃቱ የሰው ሕይወት ከመጥፋቱ ባሻገር ከ280 በላይ ምዕመናን ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ወድቀዋል።
በጥቃቱ ወቅት የምዕመናን መኖሪያ ቤቶች ተለይተው የተቃጠሉ ሲሆን፣ ንብረቶቻቸውና ከብቶቻቸውም በታጣቂዎች ተዘርፈዋል።
እንደ ሊቀ ጳጳሱ መግለጫ፣ የመቶ አንድ (101) ዓመት ረጅም ዕድሜና የታሪክ ባለቤት እንደነበረው የተገለጸው የጠላታ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሙሉ በሙሉ በእሳት እንዲወድም ተደርጓል።
በተጨማሪም የካራ ኩፍተና መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ላይ ከፍተኛ ዘረፋ የተካሄደ ሲሆን፣ በሥፍራው የነበሩ ምዕመናን ሕይወታቸውን ለማዳን የቅዱስ ጽላቱን ይዘው ለመሰደድ መገደዳቸው ታውቋል።
የጀርመን ድምፅ (ዶቼ ቬለ) ያነጋገራቸው የሀገረ ስብከቱ ሠራተኛ እንደገለጹት፣ ከጥቃቱ የተረፉት ነዋሪዎች በአሁኑ ሰዓት ወደተለያዩ አካባቢዎችና ለጊዜው ጥበቃ ወዳለባቸው አጎራባች ቀበሌዎች ከመሰደዳቸው ውጪ፣ በሰብአዊ ዕርዳታና መጠለያ በኩል ማን ሊረዳቸው እንደሚችል የታወቀ ነገር የለም።
ከግድያው ባሻገር ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናትን ማቃጠል፣ መዝረፍ እና የምዕመናን መኖሪያ ቤቶች ማውደም፤ ጥቃቱ በታቀደ መንገድ ሃይማኖትን እና ማንነትን ኢላማ ያደረገ መሆኑን ያሳያል ሲሉ ታዛቢዎችና የተጎጂ ቤተሰቦች በምሬት ይናገራሉ።
የአርሲ ሀገረ ስብከት ሚዲያ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ ማንነትና ሃይማኖትን መሠረት ባደረገው በዚህ ጥቃት በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉት 13 የክርስትና እምነት ተከታዮች ስም ዝርዝር እንደሚከተለው ቀርቧል።
- አቶ ደምረው አበራ (የ70 ዓመት)
- ከፈለኝ ልክየለው (የ56 ዓመት)
- ሐይሉ ንጉሴ (የ70 ዓመት)
- እሸቴ ዳመና (የ42 ዓመት)
5. አበባየሁ ዳኜ (የ42 ዓመት) - ሰሙ አባይነህ (የ70 ዓመት)
7. የአካባቢው ሚሊሻ (ስሙ ያልተጠቀሰ) - አማረ በላይነህ (የ80 ዓመት)
- ተሬ ደሴ (የ25 ዓመት)
- ወጣት ገነነ ጥላሁን (በሺርካ ወረዳ)
- ሙርቴሳ ጥላሁን (በሺርካ ወረዳ)
- አቶ ንጉሱ ማንደፍሮ (በሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ)
13. አቶ በቀለ ኃይለሚካኤል (በሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ) ናቸው።
ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በተፈጸመው አሰቃቂ ጥቃት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸው፣ “ኦርቶዶክሳውያኑ ተወልደው ካደጉበት፣ ወልደው ከሳሙበት ቀያቸው በሃይማኖታቸው ብቻ ቤታቸው እየተለየ ተቃጥሏል፤ ንብረታቸውና ከብቶቻቸው ተዘርፈዋል።

ከጥቃቱ የተረፉት ነዋሪዎችም ይዘውት የሸሹት እምነታቸውንና ማንነታቸውን ብቻ በመሆኑ አሁን ላይ ሜዳ ላይ ወድቀው ይገኛሉ” ሲሉ ለተጎጂዎች አስቸኳይ ዕርዳታ እንዲደረግና ጥበቃ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።
አክለውም ለሞቱት ነፍሳቸውን እንዲምር፣ ለተፈናቀሉትና ላዘኑት ደግሞ መጽናናትን እንዲሰጥ ጸሎታቸውን አድርሰዋል።
ይህ አሰቃቂ ጥቃት ይፋ መሆንን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሰፊ ሕዝባዊ ቁጭትና ተቃውሞ እየተቀሰቀሰ ይገኛል።
በተለይም በርካታ ታዛቢዎችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የመንግሥትን ጥቃቅን ዕለታዊ ውሎዎችንና ፕሮፓጋንዳዎችን ሳይቀር በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው ላይ ሲያጋሩ የሚውሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞችን አቋም በጽኑ እየተቹት ይገኛል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ብዙዎች እንደገለጹት፤ “የንጹሐን ደም እንደ ውሃ በሚፈስበት በዚህ አስከፊ ወቅት፣ እንደ ጃዋር መሐመድ ያሉ የአካባቢው ተወላጅና ተጽዕኖ ፈጣሪ የፖለቲካ ሰዎች እንዲህ ዓይነት አሰቃቂ ጭፍጨፋዎች ደጋግመው በንጹሐን ላይ ሲፈጸሙ ትንፋሽ ሲያጥራቸውና ዝምታን ሲመርጡ ማየት እጅግ የሚያስገርምና ይበልጥ የሚያሳዝን ነው።
ከዚህ በላይ ምንድነው ጉዳያችን?” በማለት ድርጊቱን በዝምታ የሚያልፉ የፖለቲካ ልሂቃንን በቁጭት ወቅሰዋል።
ይህ የልሂቃኑ ዝምታ ጥቃቱን ከማውገዝና ንጹሐንን ከማዳን ይልቅ ለፖለቲካዊ ጥቅም ሲባል እውነታን ወደ ጎን የመተው አዝማሚያ መሆኑን በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ እያስነሳ ይገኛል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጥቃቱና በተከሰተው ሰፊ ሰብአዊ ቀውስ ዙሪያ እስካሁን ድረስ ከኦሮሚያ ክልልም ሆነ ከፌዴራል መንግሥት የተሰጠ ምንም ዓይነት መግለጫም ሆነ ማብራሪያ የለም።