በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን መዋቅር ሥር የሚገኙት የዘይሴ እና የቁጫ ብሔረሰቦች፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ለማስከበር ከሚያደርጉት የህልውና ትግል ባሻገር፣ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ላይ የተፈጸመው መጠነ-ሰፊ መዋቅራዊ ማጭበርበርና የአፈና እርምጃ ሂደቱን ሙሉ በሙሉ ህገወጥ ስለመሆኑ ተነግሯል።
የምርጫ ቅስቀሳ ዕገዳንና የዕጩዎችን እንግልት ተከትሎ፣ በዕለተ-ምርጫው ከመራጮች እጅ የድምፅ መስጫ ወረቀት በኃይል እስከ መንጠቅ የደረሰ ታሪካዊ የምርጫ ወንጀል መፈጸሙን የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) ግንቦት 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ በሰጠው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርጓል።

ለWT Media የተላከው የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ በቁጫ ምርጫ ክልል የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ከተጀመረበት ሰዓት ጀምሮ በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ማለት በሚቻል ደረጃ የምርጫ አስፈፃሚዎች፣ የገዥው ብልፅግና ፓርቲ ታዛቢዎች፣ የቀበሌ አመራሮች እና የፀጥታ አካላት በመቀናጀት ከመራጩ ሕዝብ እጅ የድምፅ መስጫ ወረቀትን በኃይል ነጥቀዋል።
ምርጫውን በገለልተኝነት እንዲያስፈፅሙ የተመደቡ የምርጫ አስፈፃሚዎች ከአካባቢው የመንግሥት አካላት ጋር በጥቅም በመሳሰር፣ ከመራጩ ሕዝብ እጅ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን በኃይል በመቅማት ከሕዝብ ፍላጎት ውጭ በራሳቸው ምርጫ ለገዥው ብልፅግና ፓርቲ ድምፅ ሰጥተዋል።
መራጮች የሰጡትን የድምፅ መስጫ ወረቀት ገልጠው በማየት ቁሕዴፓን የመረጡ ዜጎችን ስም ዝርዝር በመመዝገብ ለፀጥታ አካላት አሳልፈው ሰጥተዋል።
በምርጫ ጣቢያዎች አጠገብ ቆመው ለቁሕዴፓ እና ለዕጩዎቹ ድምፅ የሚሰጡ መራጮችን የመስደብ፣ የማንጓጠጥ እና የድምፅ መስጫ ወረቀቱን በመንጠቅ በኮሮጆ ውስጥ እንዳይከቱ የማደናቀፍ ድርጊት ተፈጽሟል።
በዚህም ሳቢያ ለቁሕዴፓ ድምፅ በሰጡ መራጮች ላይ አካላዊ ጥቃት የተሰነዘረ ሲሆን፣ በቀሪዎቹ ላይ ደግሞ ከፍተኛ ዛቻና ማስፈራራት እየተፈጸመ ይገኛል በሚልም ፓርቲው በመግለጫው ገልጿል።
ፓርቲው አክለውም “በሀገራችን እስካሁን በተደረጉ ምርጫዎች የድምፅ ኮሮጆ መገልበጥ እንደሚስተዋል የሚታወቅ ቢሆንም፣ በቁጫ ምርጫ ክልል እንደ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ዓይነት ከመራጭ እጅ በኃይል የምርጫ ካርድ እና የድምጽ መስጫ ወረቀት እየተነጠቀ በመንግሥት አካላትና በአስፈፃሚዎች በመራጩ ሕዝብ ፊት ሲሰጥ በታሪክ አይታወቅም!” ብሏል።
የተፈጸሙት የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ጥሰቶች እጅግ ረቂቅነት ያላቸውና በጣት አሻራ (በፎረንሲክ ምርመራ) የሚረጋገጡ በመሆናቸው፣ ቁሕዴፓ ግንቦት 25 ቀን 2018 ዓ.ም. የተፈጸሙትን ጥሰቶች በዝርዝር በመጥቀስ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጽሁፍ ማመልከቱን አስታውቋል።
የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባንድራ በላቸው ቀደም ሲል ለWT Media እንደገለጹት፣ ፓርቲው የምርጫ ቅስቀሳ ዕገዳን፣ የፖሊስ ድብደባዎችን እና የቪዲዮ ማስረጃዎችን ለምርጫ ቦርድ በተደጋጋሚ ቢያቀርብም፣ ቦርዱ ጥፋት የፈጸመውን አካል ከመቅጣት ይልቅ “የመንደር ሽማግሌ የመሸማገል ዓይነት” ደካማ አካሄድ ሲከተል ቆይቷል።
በዚህም ምክንያት ፓርቲው ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ.ም. ጉዳዩን ወደ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመውሰድ ምርጫው እንዲታገድ ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
አሁን ላይ ከመራጩ ሕዝብ ፍላጎትና ይሁንታ ውጭ በሕገ-ወጥ መንገድ የተሰጠው ድምፅ “የቁጫ ምርጫ ክልል ሕዝብ የምርጫ ድምፅ” ተብሎ እንዳይቆጠርና ውጤቱ ሙሉ በሙሉ ውድቅ እንዲሆን ፓርቲው ሕጋዊ አቤቱታውን ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በወቅቱ አቅርቧል።
የቁጫ ምርጫ ክልል በዚህ ዓይነት ከፍተኛ የማጭበርበር ቀውስ ውስጥ በወደቀበት ማግስት፣ በጋሞ ዞን መዋቅር ሥር የሚገኘው የዘይሴ ብሔረሰብም በተመሳሳይ ሁኔታ ወታደራዊ ከበባና “የዘር ማፅዳት ዘመቻ” እየተካሄደበት መሆኑን ተወካዮች ገልጸዋል።
የዘይሴ ልዩ ምርጫ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) አባል እና የኢዜማ ዕጩ አቶ አብራሃም አሞሼ እንደገለጹት፣ የክልሉ አድማ ብተና ፖሊስ አባላት የሕዝብ ጤና ጣቢያዎችን፣ ትምህርት ቤቶችንና የቀበሌ ጽሕፈት ቤቶችን ወደ ጦር ካምፕነትና ምሽግነት ቀይረው ይገኛሉ።
የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እና የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ደሚሴ የዘይሴን ብሔረሰብ ሙሉ በሙሉ ወደ ጋሞ ብሔረሰብ ማንነት የመቀየርና መልካዓ-ምድሩን የመውረስ አጀንዳ ይዘው እየሰሩ መሆኑን የገለጹት አቶ አብራሃም፤ እስካሁን ባለው ሂደት ብቻ ከ100 በላይ ሰዎች የተገደሉበትና ከ192 በላይ ሰዎች በግፍ የታሰሩበት አስከፊ ሁኔታ መኖሩን ይፋ አድርገዋል።
ዘይሴ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ሲጸድቅ የምክር ቤቱ መሥራች ከነበሩት ብሔረሰቦች አንዱ ቢሆንም፣ የልዩ ወረዳ መዋቅር ጥያቄው በክልሉ ኃላፊዎች ሆን ተብሎ ታፍኖ መቆየቱና መዋቅራዊ አድልዎ እየተፈጸመበት መሆኑ ተገልጿል።
በሁለቱ ምርጫ ክልሎች የተፈጸመው ሁለንተናዊ መዋቅራዊ ጫና የምርጫ ሂደቱን ከዴሞክራሲያዊ መርሆዎች ውጭ ያደረገው መሆኑን የገለጹት የሁለቱ ብሔረሰቦች አመራሮች፣ በአካባቢው ሰላማዊ ሁኔታ ለመፍጠር የሚከተሉት አስቸኳይ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጥሪ አቅርበዋል።
ሕዝቡን እያሸበሩ ያሉት የክልሉ አድማ ብተና ፖሊስ፣ የጋሞ ዞን መደበኛ ፖሊስና የሚሊሻ ኃይሎች በአስቸኳይ አካባቢውን ለቀው መውጣት አለባቸው ብለዋል።
ፍፁም ገለልተኛ የሆነ ሰላም ለማስፈን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ወይም የፌደራል ፖሊስ አባላት በአስቸኳይ ሊሰማሩ ይገባል።
በተጨማሪም የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዘይሴን የልዩ ወረዳ መዋቅር ጥያቄ እንዲሁም የቁጫን የማንነት ዕውቅና ጥያቄ በአስቸኳይ ምላሽ መስጠት አለባቸው በሚል ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ዶክተር ስጦታው አረጋ በጉዳዩ ላይ ለWT Media በሰጡት አጭር አስተያየት፦ “በጋሞ ዞን ሥር በሚገኙት በእነዚህ ሁለት ብሔረሰቦች ላይ እየተፈጸመ ያለው ሁለንተናዊ መዋቅራዊ ጫና፣ የአካባቢው የምርጫ ሂደት ከዴሞክራሲያዊ መርሆዎች ሙሉ በሙሉ ያወጣውና የሕዝቡን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ መሆኑን ያሳያል።
ነፃና ገለልተኛ የሆኑ የፌደራል የጸጥታ አካላት በአካባቢው ሳይሰማሩ፣ እንዲሁም ሕገ-መንግሥታዊ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄዎች ሕጋዊ ምላሽ ሳያገኙ የሚካሄድ ምርጫ ቀውሱን ከማባባስ ባለፈ ዘላቂ ሰላምን ሊያመጣ አይችልም” ብለዋል።
WT Media በተደጋጋሚ እንደዘገበው ዘይሴ ማለት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በጋሞ ዞን መዋቅር ውስጥ የሚገኝ እና የብሔር ማንነቱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ዕውቅና ያገኘ የራሱ ልዩ እሴት ያለው ሕዝብ ቢሆንም፣ ለብሔረሰቡ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እና የራሱ መዋቅር ተከልክለው በጋሞ ዞን የዘር ማፅዳት ዘመቻ እየተካሄደበት የሚገኝ ብሔረሰብ ነው።
የቁጫ ብሔረሰብ ማለት ደግሞ በተመሳሳይ ሁኔታ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በጋሞ ዞን መዋቅር ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም፣ የብሔር ማንነቱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ዕውቅና ገና ያላገኘ የራሱ ልዩ እሴት ያለው ሕዝብ ነው። ይህ ብሔረሰብ ለማንነቱ ዕውቅና መከልከሉ ሳያንስ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እና የራሱ መዋቅር ተከልክለው በጋሞ ዞን ከፍተኛ በደል እየደረሰበት ይገኛል።
WT Media በዚህ አስቸኳይ የጋዜጣዊ መግለጫ ይዘትና በተነሱት ከባድ የምርጫ ማጭበርበር ክሶች ዙሪያ፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን የአካባቢውን ባለሥልጣናት፣ የጋሞ ዞን አስተዳደርን እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ምላሽና አስተያየት ለማካተት በተደጋጋሚ ተንቀሳቅሷል።
ሆኖም ግን ከሚመለከታቸው አካላት በኩል ስልኮችን ባለማንሳትና ፈቃደኛ አለመሆን የተነሳ ምላሻቸውን ለማግኘት የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።