GridArt_20260604_214700459

ሙሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ማህበረሰብንና የብዙዎችን ልብ ሰርስሮ የገባው የታዋቂው የባህር ዳር ከተማና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አለልኝ አዘነ የፍትሕ ሂደት ዛሬ እጅግ አሳዛኝና አስደንጋጭ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ሲራዘም የነበረው የይግባኝ ሰሚ ችሎት ዛሬ ባወጣው ውሳኔ በግድያ ወንጀሉ ጥፋተኛ ተብለው የነበሩት ግለሰቦች በነፃ እንዲለቀቁ መወሰኑን የሟች ቤተሰቦች ለ WT Media አረጋግጠዋል።

​ቀደም ሲል በጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወንጀል ድርጊቱ በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች ተረጋግጦባቸው በቅደም ተከተል የ16 እና 15 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸው የነበሩት ባለቤቱ ወ/ሮ አደይ ጌታቸው እና የእህቷ ባለቤት ሉንጎ ሉቃስ፣ በይግባኝ ሰሚው ችሎት ሙሉ በሙሉ በነፃ እንዲሰናበቱ ተወስኗል።

​ይህ ወንጀሉ በግልፅ ተረጋግጦ በነበረበት መዝገብ ላይ የተሰጠ ድንገተኛ የይግባኝ ውሳኔ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የነበረውን የመጨረሻ ተስፋ ያሟጠጠ እና ተቀባይነት የሌለው ሆኖ ተገኝቷል።

​የይግባኝ ውሳኔው በተሰማበት ወቅት በፍርድ ቤቱ ውስጥ የነበረው ውጥረት ከፍተኛ የነበረ ሲሆን የቤተሰቡ ለቅሶና ሰቆቃ መላውን የፍትሕ ናፋቂ ማህበረሰብ በእጅጉ አሳዝኗል።

ቤተሰቡ ከዚህ ቀደም ለ WT Media በይፋ ሲገልጽ እንደቆየው፣ ወንጀሉ የተፈፀመበት ቦታ አርባ ምንጭ ሆኖ ሳለ የፍርድ ሂደቱ አግባብ ባልሆነ መንገድ ወደ ዎላይታ ሶዶ እንዲዛወር መደረጉ ራሱ ለዚህ ፍርድን የማጣመም ሴራ መነሻ መሆኑን በዕንባ ያስረዳሉ።

​በተለይም በጥፋተኝነት ተፈርዶባት በነበረችው በአደይ ጌታቸው ጀርባ፣ የወቅቱን የክልሉን ባለስልጣናት የዝምድና ትስስርና ስልጣንን መከታ በማድረግ ፍርዱን በይግባኝ ለማስለወጥና ጥፋተኞችን በነፃ ለማሰናበት ሲሸረብ የነበረው የጥቅም ሴራ ዛሬ በተግባር መዋሉን የቅርብ ምንጮች በምሬት ይገልፃሉ።

ይህም ውሳኔ በሟች ንብረት (ሁለት ቤቶችና ንብረቶች) ላይ የነበረውን የፍትሐብሔር ክስ ጭምር ለማደናቀፍ የታለመ መሆኑ ይነገራል።

​ይህ ግልፅ የወንጀል ማረጋገጫ የነበረበት መዝገብ የደረሰበት ፍጻሜ በኢትዮጵያ የፍትሕ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ክርክር የሚያስነሳና በፍትሕ ተቋማት ላይ ያለውን የመተማመን ቀውስ የሚያባብስ መሆኑን የሕግ ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው።

ጉዳዩ በሰብአዊ መብት እና በሕግ የበላይነት መርህ መሠረት በከፍተኛ ደረጃ ሊጤንና ሊመረመር የሚገባው ሆኗል።

​በአሁኑ ወቅት የሟች አለልኝ አዘነ የቅርብ የቤተሰብ አባላት ሊሸከሙት በማይችሉት ድርብ ሐዘን ከፍተኛ የስነ-ልቦና ቀውስ እና ብስጭት ውስጥ ይገኛሉ።

ፍትሕን ለማድበስበስ የተደረገውን የዝምድና እና የባለስልጣናት ጣልቃ ገብነት በመቃወም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የስፖርቱ ማህበረሰብ እና የሚመለከታቸው የፌደራል የፍትሕ አካላት ከጎናቸው እንዲቆሙና ድምፃቸውን እንዲያቀናጁ ቤተሰቡ በዕንባ የታጀበ ጥሪውን ያስተላልፋል።