የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ

በ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ማግስት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ሥር በሚገኘው የቁጫ ምርጫ ክልል የተፈጸሙ መጠነ-ሰፊ የድምፅ ማጭበርበር ድርጊቶችን በመቃወም የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) የምርጫውን ውጤት ሙሉ በሙሉ ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል። 

ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እስካሁን ከቁሕዴፓ ውጭ ሌላ አቤቱታ እንዳልቀረበለት በመግለጽ፣ ማንኛውንም ዓይነት የምርጫ ቅሬታዎች በሕግ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ተቀብሎ እንደሚመረምር አስታውቋል።

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የተካሄደውን ሀገራዊ ምርጫ ተከትሎ ከቁሕዴፓ የተሰጠው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚያመላክተው፤ በምርጫ ክልሉ በሚገኙ ሁሉም ጣቢያዎች በሚባል ደረጃ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የገዥው ብልፅግና ፓርቲ ታዛቢዎች እና የጸጥታ አካላት ከመራጩ ሕዝብ እጅ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን በኃይል ሲቀሙ ውለዋል።

የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባንድራ በላቸው ቀደም ሲል ለWT Media እንደገለጹት፣ ገዥው ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳን ከማገድና የፓርቲ ጽሕፈት ቤቶችን በኃይል ከመዝጋት ባለፈ፣ በዕለተ-ምርጫው መራጮች የሰጡትን ድምፅ ገልጦ በማየት ቁሕዴፓን የመረጡ ዜጎችን ስም ዝርዝር ለጸጥታ አካላት አሳልፎ እስከመስጠት የደረሰ መዋቅራዊ ጥሰት ፈጽሟል። 

ፓርቲው ይህንን ድርጊት “ታሪካዊ የምርጫ ወንጀል” ሲል የፈረጀው ሲሆን፣ ከመራጩ ሕዝብ ፍላጎት ውጭ በሕገ-ወጥ መንገድ የተመዘገበው ድምፅ “የቁጫ ሕዝብ እውነተኛ ምርጫ” ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም በሚል ውጤቱን ሙሉ በሙሉ እንደማይቀበል በይፋ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ረቡዕ ምሽት በሰጡት ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በቁጫ ምርጫ ክልል “ምርጫ ተጭበርብሯል፣ ችግር አለ” በሚል የቀረበውን ይፋዊ አቤቱታ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ዋና ሰብሳቢዋ በቪዲዮ መግለጫቸው ላይ እንደተናገሩት፦

“የቁጫ ዲሞክራቲክ ፓርቲ አቤቱታ አቅርቦልናል፤ አቤቱታው ደርሶናል። የሕግ ክፍላችን አቤቱታውን ተመልክቶታል። የሕግ ክፍላችን የሰጠንን አስተያየት ይዘን የቀጣይ የማጣራት ሥራ ይደረጋል። በፈቃደኝነት ላይ ከተመሰረቱ ሌሎች ፓርቲዎች (ለምሳሌ ከነጻነትና እኩልነት ፓርቲ) የመጣ ነገር እስካሁን የለም።”

ዋና ሰብሳቢዋ አክለውም፣ ቦርዱ እንዲህ ዓይነት ቅሬታዎችን እና ጥያቄዎችን በሕግ እስከተቀመጠለት ጊዜ ድረስ ጠብቆ እንደሚቀበል አስታውቀዋል። በሕጉ መሠረት የምርጫ ውጤትን ይፋ የማድረጊያ ቀን እና ቅሬታ ማቅረቢያ ቀኑን ጠብቆ እስከቀረበ ድረስ፣ መስሪያ ቤታቸው ሁሉንም የሚቀርቡ ቅሬታዎች አይቶ በሕግ አግባብ መርምሮ አስፈላጊውን ውሳኔ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።

በቪዲዮው ላይ እንደተጠቀሰው እና ምርጫ ቦርድ ቀደም ሲል ባወጣው ይፋዊ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የግል ተወዳዳሪዎች ይፋዊ ቅሬታ የሚያቀርቡት ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 02 ቀን 2018 ዓ.ም. ባለው የአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ነው። ቦርዱ ይፋዊ የምርጫ ውጤትን በማዕከል ደረጃ ለመግለጽ ያቀደው ደግሞ ቅሬታ ማቅረቢያው ከተጠናቀቀ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው።

በሌላ በኩል፣ ቁሕዴፓ በበኩሉ የተፈጸሙት የሥነ-ምግባር ጥሰቶች ረቂቅነት ያላቸው በመሆኑ በጣት አሻራ እና በፎረንሲክ ምርመራ ሊረጋገጡ እንደሚገባ በመጥቀስ ግንቦት 25 ቀን 2018 ዓ.ም. ለቦርዱ በጽሁፍ ማመልከቱን ገልጿል። ፓርቲው የምርጫ አስፈጻሚዎችና የጸጥታ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ እና የተጨበረበረው የሕዝብ ድምፅ እንዲሰረዝ በሰላማዊ መንገድ ትግሉን እንደሚቀጥል አስታውቋል።

የቁጫ ብሔረሰብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን መዋቅር ሥር የሚገኝ ቢሆንም፣ ለማንነቱ ዕውቅና፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትና የራሱ አስተዳደራዊ መዋቅር ተከልክሎ በጋሞ ዞን ከፍተኛ መዋቅራዊ በደል እየደረሰበት እንደሚገኝ WT Media በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል። 

በ2013 ዓ.ም. በነበረው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ቁሕዴፓ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ አግኝቶ ማሸነፉ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን በተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ የተፈጸመው ይሄው አግላይ ተግባር አካባቢውን ይበልጥ ወደ ከፋ ቀውስ ውስጥ እንዳይከተው የፖለቲካ ምሁራን ሥጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

WT Media በቁጫ ምርጫ ክልል ከተነሱት ከባድ የምርጫ ማጭበርበር ክሶች ዙሪያ፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን የአካባቢውን ባለሥልጣናት፣ የጋሞ ዞን አስተዳደርን እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ምላሽና አስተያየት ለማካተት በተደጋጋሚ ቢንቀሳቀስም ከሚመለከታቸው አካላት በኩል ስልኮችን ባለማንሳትና ፈቃደኛ አለመሆን የተነሳ ምላሻቸውን ለማግኘት የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። ቦርዱ አቤቱታውን መርምሮ የሚሰጠውን ይፋዊ ውሳኔ WT Media በቅርበት እየተከታተለ የሚዘግብ ይሆናል።

1 thought on “ቁሕዴፓ “የምርጫ ውጤቱን አልቀበልም” አለ፤ ቦርዱ “ቅሬታዎችን በሕግ አግባብ እመረምራለሁ” ሲል አስታወቀ”

Comments are closed.