1000114393

በተጫዋች አለልኝ አዘነ የግድያ መዝገብ ላይ ቀጠሮው በድጋሚ ተራዘመ

በታዋቂው የባህር ዳር ከተማና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አለልኝ አዘነ የግድያ መዝገብ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዎላይታ ምድብ ችሎት ዛሬ ግንቦት 13 ቀን 2018 ዓ.ም የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ቢጠበቅም ችሎቱ በድጋሚ ቀጠሮውን በማራዘም ለግንቦት 27 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ይህንን ጉዳይ ከመጀመሪያው ጀምሮ በቅርበት ሲከታተል የቆየው WT Media ዛሬ በፍርድ ቤቱ ቅጥር ጊቢ ውስጥ የተፈጠረውን ልብ ሰባሪ ክስተትና የቤተሰቡን ሰቆቃ በቅርብ ምንጮቹ አረጋግጧል።

​ውሳኔ ይሰጣል በሚል ተስፋ ከአርባ ምንጭና ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡት የሟች አለልኝ አዘነ ቤተሰቦች፣ ቀጠሮው ለሶስተኛ ጊዜ መራዘሙን ሲሰሙ ከፍተኛ የስነ-ልቦና ስብራት ደርሶባቸዋል።

​”መዝገቡ አሁንም ተሰርቶ አላለቀም” በሚል ምክንያት ቀጠሮው ወደ ግንቦት 27 መዛወሩን ተከትሎ፣ የተጎጂ ቤተሰቦች በፍርድ ቤቱ ቅጥር ጊቢ ውስጥ በዕንባ ተንከባለው ጩኸታቸውን አሰምተዋል።

​ቤተሰቦቹ በከፍተኛ ሀዘንና ምሬት ውስጥ ሆነው “ያለ ጥፋታችንና ያለ ፍላጎታችን ተጎጂ ሆነን ያላስፈላጊ ወጪ እያወጣን ነው። ቢያንስ መንግስት የለም እንዴ? ይህንን ግፍ መንግስት ማየት አይችልም?” ሲሉ በዕንባ የታጀበ ድምፃቸውን ለሕዝብና ለመንግስት አሰምተዋል።

​መዝገቡ ገና ከመጀመሪያው ጀምሮ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከአርባ ምንጭ ወደ ዎላይታ ሶዶ መዛወሩ ሳያንስ፣ አሁን ደግሞ በተደጋጋሚ የሚሰጠው የችሎት ቀጠሮ መራዘም በቤተሰቡ ላይ ሊሸከሙት የማይችሉትን የኢኮኖሚ ጫና ፈጥሯል።

​የሀገሪቱን ወቅታዊ የትራንስፖርት ውድነትና የነዳጅ እጥረት ተቋቁመው፣ ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ እያደረጉ ከአርባምንጭ ወደ ዎላይታ ሶዶ በተደጋጋሚ እንዲመላለሱ መደረጉ ፍትሕን ለማድበስበስና ቤተሰቡን ለከፍተኛ ድካም ለመዳረግ የታቀደ ይመስላል ሲሉ የቅርብ ወገኖች በምሬት ይናገራሉ።

​የአለልኝ አዘነ ቤተሰቦች በአሁኑ ወቅት እጅግ በጣም አስገዳጅና አሳሳቢ ሁኔታ ላይ በመሆናቸው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና ሌሎች የሚዲያ ተቋማት ድምፅ እንዲሆኑላቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የባህር ዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች በነበረው አለልኝ አዘነ ግድያ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙት ባለቤቱ አደይ ጌታቸው እና የእህቷ ባለቤት ሉንጎ ሉቃስ በጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎባቸው የነበረ መሆኑ ይታወሳል።

ፍርድ ቤቱ በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች ወንጀሉን ማረጋገጡን በመግለፅ በአደይ ጌታቸው ላይ የ16 ዓመት፣ በሉንጎ ሉቃስ ላይ ደግሞ የ15 ዓመት ጽኑ እስራት መፍረዱ አይዘነጋም።

​ሆኖም አሁን ላይ ይግባኝ ሰሚው ችሎት መዝገቡን ከአርባ ምንጭ ወደ ዎላይታ ሶዶ ያዛወረበት አግባብ እና ውሳኔ ለመስጠት በተደጋጋሚ የሚቀያይራቸው ቀጠሮዎች ከጀርባው የባለስልጣናት እጅ እንዳለበት ፍንጭ የሚሰጥ ነው ሲሉ ቤተሰቦቹ ይከሳሉ።

በጥፋተኝነት የተፈረደባት የአደይ ጌታቸው ወገኖች የወቅቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፍርድቤት ፕሬዝዳንት የቅርብ የዝምድና ትስስርና የባለስልጣናትን ስልጣን መከታ በማድረግ የተፈረደባቸውን የነፍስ ማጥፋት ወንጀል ውሳኔ በማድበስበስ በነፃ ለማሰናበትና ፍርዱን ሙሉ በሙሉ ለማጣመም ከፍተኛ ሴራ እየተሸረበ ነው” በሚል ቅሬታ እያቀረቡ ነው።

​የተጎጂ ቤተሰቦችም ሆኑ የሕግ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ ጉዳዩን በቅርብ ባለ ገለልተኛ ችሎት ማየት እየተቻለ በድብቅ ደብዳቤ ወደ ዎላይታ መላኩ እና አሁን ደግሞ በድጋሚ ለግንቦት 27 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱ ቤተሰቡን ለከፍተኛ እንግልት በመዳረግ ጉዳዩን ከአንገት በላይ ለማድረግና ጥፋተኞችን ለማስመለጥ የተወጠነ የጥቅምና የዝምድና ትስስር ውጤት መሆኑን በዕንባ በመግለፅ የፌደራል መንግስትና የሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት ጣልቃ እንዲገቡ በአፅንኦት እየጠየቁ ይገኛሉ።

WT Media የጀመረውን ሂደቱን መከታተልንና ፍትሕ እስኪረጋገጥ ድረስ ይህንን ተከታታይ ዘገባ ለሕዝብ ማድረሱን አያቋርጥም።

​🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media