ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ ያስቆጠረውና በዎላይታ ሶዶ ከተማ የኦሞ ሸለቆ ሆቴል ባለቤት በነበሩት በአቶ ላቁ ማሊሞ ላይ የተፈጸመውንና ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን መጠነ-ሰፊ የፍትሕ እጦት አሁንም ድረስ በፍትሕ ሥርዓቱ መዋቅራዊ እንግልትና በሰነዶች መጥፋት ሰበብ ምላሽ ሳያገኝ መቆየቱን WT Media ከ3 ወራት በፊት መዘገቡ ይታወሳል።
ይህንን ተከታታይ ዘገባ መነሻ በማድረግ፣ በዜጎች ሕጋዊ ይዞታ ላይ የሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀትና በጥቅም በመሻረክ ወንጀል የተሳተፉ የማዘጋጃ ቤት ባለሙያዎችና ግለሰቦች ከ20 ዓመታት በኋላ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የተናገረ ትልቅና በጎ ጅምር ሆኖ ተመዝግቧል።
ይሁን እንጂ ጉዳዩ አሁን ላይ ወደ አዲስና ጠንከር ያለ የሕግና የምርመራ ምዕራፍ መሸጋገሩን የሚያሳዩ አዳዲስ መረጃዎችና የሰነድ ማስረጃዎች ለ WT Media ደርሰዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ በአካባቢው የሚገኘው የ WT Media ምንጭ በምስጢር ያሰባሰበው ዝርዝር የድምፅ መረጃ እና ከተበዳዩ ወገን የተገኙ የፍርድ ቤትና የፖሊስ ሰነዶች እንደሚያመለክቱት፣ የሰነዶቹ መጥፋት ተራ የአሠራር ስህተት ሳይሆን የከበደ የሙስና እና የሀሰተኛ ሰነድ ዝግጅት ወንጀል ውጤት እንደሆነ ጥርጣሬዎችን አበርትቷል።
ለ WT Media በቅርብ የደረሱት ይፋዊ ሰነዶች እንደሚያስረዱት በአቶ ላቁ ማሊሞ ይዞታ ላይ የተፈጸመው በደል ከንብረት ክፍፍል መዝገብ መጥፋት ባለፈ፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በቀጥታ የተሳተፉበት መጠነ-ሰፊ የሀሰተኛ ሰነድ ማዘጋጀት ወንጀል እንደሆነ ያሳያል።
በሰነዶቹ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው የአመልካች አቶ ስምኦን ጫሬ (የአቶ ላቁ ወኪል/ተበዳይ) አድራሻ ዎላይታ ሶዶ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ኢ/ምህረት ቀበሌ ሲሆን፣ በሳይት ቁጥር A1778/08 ስፋቱ 396 ካሬ ሜትር በሆነውና ከ1967 እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ ግብር ሲከፈልበት በነበረው ሕጋዊ የመኖሪያ ቤት ይዞታ ላይ የሀሰት ሰነድ ተዘጋጅቶበታል።
የአራዳ ቀበሌ ማዘጋጃ ቤት መሐንዲሶች የሆኑት 1ኛ. አቶ እንየው ኢየሱ፣ 2ኛ. አቶ ደምሴ ደሳለኝ እና 3ኛ. አቶ ግርማ ጌጠና ከተባሉ ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር አመልካች በሌለበትና በማያውቀው ሁኔታ በይዞታው ላይ የሀሰት ሳይት ፕላን በማዘጋጀት መሬቱን “ግራም አለማየሁ” ለተባለ ሌላ ግለሰብ አሳልፈው ሰጥተዋል።


ይህንን ተከትሎ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምግብ ምርመራ ዘርፍ በቁጥር 4348/009/23/18 በተጻፈ ደብዳቤ ጉዳዩን መርምሮ ሪፖርት እንዲያደርግ ለሶዶ ከተማ ፖሊስ መመሪያ አስተላልፏል። በዚህም መሠረት የዎላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ ታክቲካዊ ምርመራ ዲቪዥን ኃላፊ ተጠርጣሪዎቹ ተይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
በዚሁ የምርመራ ሂደት ውስጥ WT Media ያወጣውን ተከታታይ ዘገባ መነሻ በማድረግ በቁጥጥር ሥር ሳይውሉ የቆዩትና የዜጎችን ሕጋዊ ይዞታ በሀሰተኛ ሳይት ፕላን ለሌላ አካል አሳልፈው የሰጡ የጥቅም ተጋሪዎችና የማዘጋጃ ቤት ባለሙያዎች አሁን ላይ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቋል።


ይህ ከ20 ዓመታት መዋቅራዊ በደልና እንግልት በኋላ የተወሰደው እርምጃ ተጠያቂነትን ለማስፈንና ለቀጣዩ የሕግ የበላይነት ሂደት እጅግ በጎ ጅምር ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ሆኖም ግን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ብቻውን ፍጹም የፍትሕ መረጋገጥ ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተለው የ WT Media የምስጢር ምንጭ ባደረሰን መረጃ መሠረት፣ በጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም የምርመራ መዝገቡ ተይዞ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው የነበረ ቢሆንም፣ በወቅቱ በዋስ እንዲፈቱ መደረጉ ይታወሳል።
ምንጫችን አክሎ እንደገለጸው የቀጠሮው ሁኔታ እያተራመሰ ይገኛል። መጀመሪያ ቀጠሮው ጥቅምት 13 ላይ የነበረ ቢሆንም ችሎቱ ቀጠሮውን አራዝሞ ወደ ሰኔ 1 ቀን አሻግሮታል። የሕግ ባለሙያዎችን በገንዘብ በመግዛት፣ ፍትሕ እንዳይሰፍን መዝገቡን በገንዘብ የመዝጋትና የማድበስበስ ከባድ የሙስና ሁኔታ እየተሰማ ይገኛል። የክልል ፍርድ ቤት ያሉትን አካላት እንኳ በአግባቡ መያዝ አልተቻለም።
ስለሆነም አሁንም ድረስ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ያለው ድብቅ የጥቅም ትስስርና መዝገብ የማድበስበስ ሙከራ ሙሉ በሙሉ ስላልተበጠሰ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ከፍተኛ የፍትሕ አካላት ሂደቱን በጥብቅ ሊከታተሉት ይገባል። ዋናውና ቁልፉ ተግባር ሂደቱ ከማንኛውም ጣልቃ ገብነት የጸዳ ሆኖ፣ ፍርድ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ገለልተኛና ተገቢ የሆነ ውሳኔ እንዲሰጡ ማድረግ ላይ ነው፤ ለዚህም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የፖሊስ ኮሚሽን ቁርጠኝነት አሁንም ድረስ በጥብቅ ይጠበቃል።
ይህ የአቶ ላቁ ማሊሞ ጉዳይ የአንድ ግለሰብ ወይም የአንድ ቤተሰብ ብቻ ተነጥሎ የሚታይ የፍትሕ እጦት ታሪክ አይደለም። ይህ ክስተት በአካባቢው በየደረጃው ባሉ ማዘጋጃ ቤቶችና የፍትሕ መዋቅሮች ውስጥ ባለው ክፍተት ሳቢያ በርካታ ድምፅ አልባ ዜጎች በየቀኑ እየገጠማቸው ስላለው መጠነ-ሰፊ የፍትሕ መጓደልና የበደል አረንቋ ትልቅ ማሳያና ማረጋገጫ እንደሆነ በርካቶች እየገለፁ ይገኛሉ።
WT Media ለዚህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሰጠበትና እስከ መጨረሻው ድረስ በጽናት የሚከታተልበት ዋናው ምክንያትም ይኸው ነው፤ ይኸውም የአንድን ግለሰብ መብት በማስከበር ሂደት ውስጥ የአጠቃላይ ማኅበረሰቡን የፍትሕ መጓደል ሥር የሰደደ ችግር ይፋ ለማውጣትና ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ስለሚፈልግ ነው።
የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔን (በመዝገብ ቁጥር 24782) ወደ ጎን በመተው የአሠራር ለውጥንና የመዝገብ ቤት ዝውውርን ሰበብ በማድረግ ፍትሕን ከ20 ዓመታት በላይ ማገት በአደባባይ የተፈጸመ የሕግ ሥርዓት ውድቀት ነው። አሁን ላይ ደግሞ በማዘጋጃ ቤት ባለሙያዎች ጭምር ተባባሪነት የዜጎችን ይዞታ በሀሰተኛ ሰነድ የመቀማት ወንጀል መጋለጡ የጉዳዩን አሳሳቢነት ይበልጥ ያጎላዋል።
WT Media ጉዳዩን እስከ መጨረሻው በቅርበት መከታተሉን የሚቀጥል ሲሆን፣ የተራዘመውን የሰኔ 1 2018 ዓ.ም ቀጠሮ ተገን በማድረግ የምርመራ መዝገቦች እንዳይደገፉና ተጠርጣሪዎች በሕግ ፊት ቀርበው ገለልተኛ ፍትሕ እንዲያገኙ፣ እንዲሁም ለአቶ ላቁ ማሊሞና ለቤተሰቦቻቸው በአስቸኳይ ይፋዊ ምላሽና ፍትሕ እንዲሰጥ በጥብቅ ይጠይቃል። የፍትሕ መዘግየት ፍትሕን እንደመንፈግ ይቆጠራል! ጉዳዩን መከታተላችንን እንቀጥላለን።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፥ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media