GridArt_20260609_163904336

​ለአንድ መቶ ዓመታት ያህል ለዎላይታ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የአጎራባች አካባቢዎችን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ነፍስ ሲታደግ የቆየው ታሪካዊው የኦቶና ሆስፒታል ምክንያቱ ባልታወቀ የእሳት አደጋ ከወደመ በኋላ በሚመለከታቸው አካላት ትኩረት መነፈጉ በአካባቢው ላይ እጅግ አስደንጋጭ ሰብዓዊ ቀውስ እያስከተለ ይገኛል።

“ኦቶና ሆስፒታል ታመመ፤ እናክመው!” በሚል መሪ ቃል የደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ጥላሁን ከበደ ለሆስፒታሉ መልሶ ግንባታ ይፋዊ ጥሪ ካስተላለፉ እነሆ መጪው ሐምሌ 19 ቀን 2018 ዓ.ም አንድ ዓመቱን ይደፍናል።

ሆኖም እስካሁን ድረስ ሆስፒታሉ መልሶ መገንባት ቀርቶ ለሆስፒታሉ ተብሎ የተሰበሰበው ገንዘብና ቁሳቁስ የት እንደደረሰ ግልጽ ባለመሆኑ እና የባለሥልጣናቱ ቸልተኝነት በመበርታቱ በሕብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ እየተቀሰቀሰ ይገኛል።

​የኦቶና ሆስፒታል በእሳት አደጋ መውደሙን ተከትሎ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና በሕዝባዊ የጤና መድህን አገልግሎት ያገኙ የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለከፍተኛ ችግርና መከራ ተጋልጠዋል።

የጤና መድህን ተጠቃሚ የሆኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችና አቅመ-ደካሞች ብቸኛ አማራጫቸው ኦቶና ሆስፒታል በመሆኑ ሆስፒታሉ ከወደመ ወዲህ ወደ ግል ሕክምና ተቋማት ሄደው ለመታከም ፍጹም የገንዘብ አቅም አጥተዋል።

​ይህንን ተከትሎ ወደ ግል ተቋማት መሄድ የማይችሉ ምስኪን ዜጎች ቤታቸው ቁጭ ብለው ለሞትና ለተለያዩ የከፉ የጤና እክሎች ተዳርገዋል።

በአካባቢው ያሉ ሌሎች የመንግሥት ጤና ተቋማት ደግሞ የኦቶናን ሰፊ የሕክምና ጫና መሸከም ባለመቻላቸው፣ በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ በአልጋና በባለሙያ ዕጦት በየሆስፒታሉ ኮሪደር ላይ እየተንገላታ ይገኛል።

ታክመው መዳን የሚችሉ ቀላል ሕመሞች ሳይቀር፣ የሪፈራል ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ በመናጋቱ ምክንያት ወደ ከፋ ደረጃ ተቀይረው የዜጎችን ሕይወት በየቀኑ እየቀጠፉ ይገኛሉ።
​
​WT Media የዘርፉን ባለሙያዎች በማሳተፍና መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በመፈተሽ ያደረገው ልዩ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያመለክተው ሆስፒታሉ አገልግሎት ማቋረጡን ተከትሎ እስካሁን ድረስ በየቤቱና በየቀበሌው የሞቱ ዜጎች ቁጥር ከ3 ሺህ በላይ እንደሚሆን ይገመታል።

ይህ አስደንጋጭ እልቂት በይፋ ባይመዘገብም የማኅበረሰቡን የጤና ዋስትና ክፉኛ ያናጋና ዝምታ የታከለበት ብሔራዊ አደጋ ሆኗል።

​ይህ ሰብዓዊ እልቂት በየቀኑ እየጨመረ ባለበት ሁኔታ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና የዎላይታ ዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ለዚህ አንገብጋቢና የሚሊዮኖች ሕይወት ለሚቀጠፍበት ጉዳይ የሰጡት ትኩረት እጅግ አነስተኛ መሆን በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ምሬት ፈጥሯል።

የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ጥላሁን ከበደ “እናክመው” በሚል የገቡት የተስፋ ቃል አንድ ዓመት ሊሞላው ቢቃረብም የተሰበሰበው የሕዝብ ሀብትና ቁሳቁስ የት እንደደረሰ ይፋ ባለማድረግ ለጉዳዩ ግድየለሽ መሆናቸውን አሳይተዋል።

ባለሥልጣናቱ ግንባታው በተጨባጭ የሚጀመርበትን የተቆረጠ ቀን ከመናገር ይልቅ በየጊዜው በ”ተስፋ ቃል” ማራዘማቸው የሕዝብን ሕይወት ቸል ማለታቸውንና ጉዳዩን ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ እንደተጠቀሙበት ማረጋገጫ ሆኗል።

​የሆስፒታሉን መልሶ ግንባታ መዘግየት በተመለከተ ባለፉት ወራት ከተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የተሰጡ መግለጫዎች በ”ተስፋ ቃል” ላይ ብቻ የተንጠለጠሉና መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ግንባታ ያላገዙ መሆናቸውን WT Media ያደረገው ተከታታይ ክትትል ያሳያል።

​ከአምስት ወራት በፊት የዎላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ የወደመውን ክፍል መልሶ ለመገንባት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ፕሮጀክቱ ውሳኔ አግኝቶ ወደ ሥራ የመግቢያ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ እና ግንባታው በሕዝብ ተሳትፎና በመንግሥት ድጋፍ እንደሚከናወን አስታውቀው ነበር።

ሆኖም ዋና አስተዳዳሪው ግንባታው መቼ እንደሚጀምርና መቼ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የገለጹት የተቆረጠ ቀን አልነበረም።

​ከአራት ወራት በፊት ደግሞ፣ የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጉቼ ጉሌ ከወራት ዝምታ በኋላ በሰጡት ማብራሪያ ግንባታውን ለመጀመር ከፌዴራል ገንዘብ ሚኒስቴር “መልካም ቃል” መገኘቱን ጠቅሰው በሚቀጥሉት ከ8 እስከ 10 ወራት ውስጥ ሆስፒታሉ ተጠግኖ ሙሉ አገልግሎት እንደሚሰጥ ቃል ገብተው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ ሆስፒታሉ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች (ሀዋሳ፣ አርባ ምንጭ፣ ዲላ፣ ጅንካ) እና ከክልሉ መንግሥት በተገኙ “ቁርጥራጭ” የሕክምና መሣሪያዎች ድጋፍ በከፊል አገልግሎት መቀጠሉን ቢገልጹም ይህ ዓይነቱ ድጋፍ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብን ፍላጎት ሊያሟላ እንደማይችልና በአሁኑ ወቅት ሆስፒታሉ ለሕዝቡ የሚሰጠው አገልግሎት እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ከታካሚዎች የሚደረሱ ቅሬታዎች ያረጋግጣሉ።

ዛሬም ድረስ ተጨባጭ ግንባታ አለመጀመሩ የሕዝቡን ስጋት ይበልጥ አባብሶታል። WT Media ያነጋገራቸው ታካሚዎች “እስከዚያ በተስፋ ቃል እስከሚገነባ ድረስ ስንቱ ሕመምተኛ በግል ሆስፒታሎች ውድ ክፍያና በጤና አገልግሎት እጦት ሕይወቱ ያልፋል?” ሲሉ በምሬት ይጠይቃሉ።

​ሆስፒታሉ በወደመ ማግስት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ከዜጎችና ከተለያዩ ወገኖች ከፍተኛ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ መሰብሰቡ በይፋ ቢነገርም የተሰበሰበው ሀብትና የገንዘብ መጠን ለሕዝብ ግልጽ አለመደረጉም ከፍተኛ ቅሬታ ፈጥሯል።

መልሶ ግንባታው በምን ደረጃ ላይ እንዳለና ለምን እንደቆመ የሚሰጥ ይፋዊ መግለጫ ባለመኖሩ ጉዳዩ “የፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ነበር ወይ?” የሚል ከባድ ጥርጣሬ በማኅበረሰቡ ዘንድ አሳድሯል።

​የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የክልሉና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች የሚከተሉትን አስቸኳይ እርምጃዎች እንዲወስዱ በጥብቅ እያሳሰቡ ይገኛሉ።

​እስካሁን ድረስ ለኦቶና ሆስፒታል መልሶ ግንባታ ከተለያዩ ወገኖች የተሰበሰበው የገንዘብና የቁሳቁስ መጠን ለሕዝብ በይፋና በግልጽ እንዲታወቅ ​የሆስፒታሉ መልሶ ግንባታ በተጨባጭ የሚጀመርበት የተቆረጠ ቀንና የጊዜ ሰሌዳ ተለይቶ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ ይጠይቃሉ።

በተጨማሪም ​ግንባታው ተጠናቆ ሆስፒታሉ ሙሉ አገልግሎት መስጠት እስከሚጀምር ድረስ በጤና መድህን ለሚታከሙ ምስኪን ዜጎች አማራጭ የሕክምና ቦታና ምቹ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲመቻች እና ​የመንግሥት ኃላፊዎች ለሕዝብ የገቡትን ቃል እንዲያከብሩና አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጡ በአፅንኦት በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።

እንደ አስተያየት ሰጪዎች ገለፃ ​የኦቶና ሆስፒታል መውደም “የአንድ ተቋም ሕንፃ መጥፋት ብቻ ሳይሆን የሚሊዮኖች የሕይወት ዋስትና መቃጠል ነው። የሰው ሕይወት በፖለቲካዊ ቸልተኝነት፣ በተስፋ ቃላት ማራዘም እና በምዝበራ ስጋት ሊቀጠፍ አይገባምም” ይላሉ።

​አክለውም የፌዴራል መንግሥትና የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ይህንን መዋቅራዊ ቸልተኝነትና እየደረሰ ያለውን እልቂት እንደ ብሔራዊ አደጋ በመቁጠር በአስቸኳይ ጣልቃ ገብነት በማድረግ ለሆስፒታሉ መልሶ ግንባታ ቀጥተኛ አመራርና በጀት እንዲመድቡና የተሰበሰበው የሕዝብ ሀብት ኦዲት ተደርጎ መልሶ ግንባታው በአስቸኳይ እንዲጀመር ተጠይቋል።