በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ወቅታዊና አንገብጋቢ የሆነ የማህበረሰብም የመንግስትም ትልቁ ችግር የሰዎች ህገወጥ ፍልሰት ነው ያሉት ዶክተር ታገሰ አቦ የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ፤ የልማትና ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር መምህርና ተመራማሪ እንደ አንድ ከፍተኛ ተቋም የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ በግንባር ቀደምነት መፍትሔ አምጪነት መስራቱን ጠቁመዋል።
እንደ ደቡብ ብሔራዊ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስትና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ይሄንን የሰዎች ፍልሰትና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት ባለፉት አምስት አመታት የተሰሩ ስራዎች ምን ለውጥ አመጡ የሚለውን ጥልቅ ምርምር በማድረግ ለዘላቂ መፍትሔ ዩኒቨርስቲው ሰርቷል ብለዋል።
ከእነኚህ አንዱ ከስደት ተመላሾችን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችንና ለስደት ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ስጋት የተጣለባቸው የማህበረሰብ ክፍሎችን ተደራሽ የሚያደርግ የፕሮጀክት ሰነድ በማቅረብ የመልሶ ማቋቋሚያ ፖይሌት ፕሮግራም ከአመት በፊት መደራጀት ነው።
ፕሮጀክቱ እንደመነሻነት በአረካ ከተማ መስተዳደር ከሀምሳ በላይ አባላትን ያቀፈ ማህበር በስራ እድል ፈጠራ ሲያቋቁም በዋናነት የገቢ ማመንጫ ማሻሻሉ ላይ ትኩረቱን አድርጓል።
ጎን ለጎን በአከባቢ ጥበቃ ስራ ላይ እንዲሰማሩ በቃጫ ምርት ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት በመቅረፅ በአረካ ከተማ ከመንግስት በተሰጠ አስር ሄክታር መሬት ላይ የቃጫ ዛፍ በመትከልና በመንከባከብ ምርታማ እንዲሆኑ ተሰርቷል።
እንደሀገርም እንደ አለምም ተፈላጊ የሆነ ጥራት ያለው የተፈጥሮ ቃጫ ማህበሩ ሲያመርት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር የገበያ ትስስርም ተመቻችቶላቸዋል።
ከዚህም ጎን ለጎን የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሆነው ማህበር አባላት አስቸኳይ የኢኮኖሚ ድጎማ እንዲያገኙ የጎንዮሽ ቢዝነስ በመፍጠር የዶሮ እርባታ፣ የጓሮ አትክልትና የመሳሰሉ ስራዎች ላይ በመሰማራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት አምጪ የገቢ ምንጭ መቀየሱን ነው ዶክተር ታገሰ አቦ የሚገልፁት።
ይሄንን ስራ ለማሳለጥ የግንዛቤ ማሳደጊያና የምክክር መድረክ በፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች በባለድርሻ አካላትና በፕሮጀክቱ ታቅፈው በተደራጁ የመልሶ ማቋቋሚያ ማህበር አባላት መካከል ተደርጓል።
በመድረኩ የፕሮጀክቱ እንቅፋት ናቸው የተባሉ ጉዳዮች በአባላቱና በባለድርሻ አካላት ተነስተው መፍትሔ ጠቋሚ ውይይት መደረጉን ከዩኒቨርስቲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ዝርዝር ወቅታዊ፣ ትኩስ እንዲሁም ሚዛናዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ዌብሳይት
www.wolaitatimes.com.et
ፌስቡክ፡-
https://www.facebook.com/wolaitatime/
ቴሌግራም፦
https://telegram.me/Kiikiya
ዩቲዩብ፦
https://m.youtube.com/channel/UCQy9hoOijiE8FStts2SmtXw?noapp=1
በመጠቀም መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል።
Wolaita Times, 01/12/13 E.C , Sodo, Ethiopia🇪🇹


