የፌዴራል መንግሥት ለ2019 በጀት ዓመት ለክልሎች ያዘጋጀውን የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ መጠን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ላይ የታየው የበጀት ድልድል ማነስ በሰነድ ማስረጃዎች የታገዘ ሰፊ ቅሬታና ክርክር እየቀሰቀሰ ይገኛል።
ለ WT Media በደረሱት ይፋዊ የሰነድ ምስሎች መሠረት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ካለው የወንበር ቁጥር (የሕዝብ ውክልና) አንጻር ተመጣጣኝ ያልሆነና ፍትሐዊነት የጎደለው የበጀት ድልድል መደረጉ ታይቷል።
በሀገሪቱ የፌዴራል በጀት ድልድል ቀመር በዋናነት በሕዝብ ቁጥር ላይ ተመስርቶ የሚሰላ መሆኑ ይታወቃል።


ይህ መርህ በኦሮሚያ ክልል (178 ወንበሮች – 1ኛ በጀት) እና በአማራ ክልል (138 ወንበሮች – 2ኛ በጀት) ላይ በትክክል ተተግብሯል።
ነገር ግን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበር ብዛት (በሕዝብ ቁጥር መነሻነት) ከአማራና ኦሮሚያ ቀጥሎ በሀገሪቱ በ3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በበጀት ድልድሉ ላይ ግንባር ቀደም ተጎጂ ሆኗል።
ለዚህም እንደ ግልጽ ማሳያ የተጠቀሰው የሚከተለው ንጽጽር ነው፦
በምስል ላይ ባለው ይፋዊ የውክልና ሰነድ መሠረት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክር ቤቱ 49 ወንበሮች ሲኖሩት የሶማሌ ክልል ደግሞ 23 ወንበሮች አሉት። ደቡብ ኢትዮጵያ በሕዝብ ውክልና ቁጥር በ26 ወንበሮች እጅግ ሰፊ ብልጫ አለው።
ይሁን እንጂ በምስል ላይ ባለው የበጀት ሰነድ መሠረት፣ የሶማሌ ክልል 51,944,000,572 (ከ51.9 ቢሊዮን በላይ) ብር ሲመደብለት፣ ከግማሽ በላይ የሕዝብ ውክልና ወንበር ብልጫ ያለው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግን 36,589,812,025 (ከ36.5 ቢሊዮን በላይ) ብር ብቻ ተመድቦለታል።
ይህ የ15.3 ቢሊዮን ብር ሰፊ ልዩነት፣ የበጀት ድልድል ቀመሩ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ላይ በተገቢው መንገድ አለመተግበሩንና የታየውን መዋቅራዊ የበጀት ኢፍትሐዊነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ማረጋገጫ ሆኗል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በርካታ የሥራ አጥ ቁጥር፣ ያልተጠናቀቁና የተጓተቱ ፕሮጀክቶች እንዲሁም ከፍተኛ የድህነት ጫና ያለበት መሆኑ እየታወቀ፣ እንዲህ ዓይነቱ የበጀት መገለል መፈጠሩ የአካባቢውን ምሁራንና ታዛቢዎች አስቆጥቷል።
ይህ ኢፍትሃዊነት ግን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፊት አመራሮች የክልሉን የልማትና የሕዝብ ጥቅም ለማስከበር በፌዴራል ደረጃ ጠንካራ ክርክርና ሙግት ማድረግ አለመቻላቸውን ታዛቢዎች በሰፊው እየተቹት ይገኛል።
ሀገራዊ ጥሪ በሚኖርበት ጊዜ ሁሉ ከፍተኛ የሰው ኃይልና የቁሳቁስ ግብር የሚከፍለውን ሕዝብ ጥቅም ማስከበር አለመቻል የክልሉን አመራሮች የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤትንና የፋይናንስና ፕላን ልማት ቢሮን በታሪክ ፊት ተጠያቂ ያደርጋቸዋል ተብሏል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምሁራን፣ ወጣቶችና አጠቃላይ ማኅበረሰቡ ይህንን በይፋዊ ሰነድ የተደገፈ የበጀት ልዩነት በመረዳት፣ ክልሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ፍትሐዊ ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥና መብቱ እንዲከበር በጋራና በአንድነት ሊሟገቱ እንደሚገባ ጥሪዎች እየቀረቡ ነው።
WT Media የዚህን የበጀት ድልድል ሕጋዊ መሠረትና የክልሉ አመራሮች የሚሰጡትን ተቋማዊ ምላሽ ተከታትሎ መረጃዎችን ማድረሱን ይቀጥላል።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media