በዛሬው ዕለት በተካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 25ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ፣ የምክር ቤቱ አባላት በፌዴራል መንግሥት የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል። በዚህ በጀት ላይ ከዎላይታ ዞን የተወከሉት የሕዝብ ተወካይ የሆኑት ወይዘሮ እታገፈራዉ ሞታ ለአንድ ክፍለ ዘመን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ነፍስ ሲታደግ ቆይቶ በእሳት አደጋ የፈረሰውን የኦቶና ሆስፒታልን ወቅታዊ አሰቃቂ ቀውስ እና የመልሶ ግንባታ መዘግየትን በተመለከተ በምክር ቤቱ መድረክ ላይ ጥያቄ አቅርበዋል።
ይህንን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ የተወካይ እታፈራው ሞታን እርምጃ የሚያደንቁና ጉዳዩን የሕዝብ ድምፅ ማስተጋባት አድርገው የሚመለከቱ አስተያየቶች በስፋት እየተንጸባረቁ ይገኛሉ። ቪዲዮ ጉዳዩን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ከሠራናቸው የምርመራ ዘገባዎች እና ከሕዝብ ውክልና ተቋማዊ ኃላፊነት አንጻር የሚከተለውን ጋዜጣዊ ትንተና ያቀርባል።
ተወካይ እታፈራው በምክር ቤቱ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የኦቶና ሆስፒታል መውደም በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ እያስከተለ ያለውን መጠነ-ሰፊ የጤና አገልግሎት እጦት በመጥቀስ የፌዴራል መንግሥትና የገንዘብ ሚኒስቴር ለሆስፒታሉ መልሶ ግንባታ አስቸኳይ ትኩረትና የበጀት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ይህ ድምፅ በአምስት ዓመቱ የውክልና ዘመን ማብቂያ ላይ የተሰማ በመሆኑ በተለያዩ የአካባቢው ታዛቢዎች ዘንድ “የዘገየ ቢሆንም ሊበረታታ የሚገባው የሕዝብ እሮሮ ነጸብራቅ” ተደርጎ ተወስዷል።
ይሁን እንጂ የሕዝብ ተወካዮች ከዚህ ቀደም በአካባቢው ላይ የደረሱ ሰብዓዊ ቀውሶችን በወቅቱና በተጠናከረ መልኩ ከማንሳት አንጻር የነበረባቸው ተቋማዊ ክፍተት በሕዝቡ ዘንድ አሁንም ለሚነሱ ቅሬታዎች መነሻ መሆኑን የሚዲያችን ዳሰሳ ያመለክታል።
ዛሬ በምክር ቤት የተነሳው የኦቶና ሆስፒታል ጉዳይ WT Media መሬት ላይ ወርዶ በዳሰሳ ጥናትና በዘርፉ ባለሙያዎች እገዛ በተደጋጋሚ ተከታታይ የምርመራ ዘገባዎችን የሠራበት አንገብጋቢ ብሔራዊ አደጋ ነው።
የሚዲያችን የምርመራ ቡድን ባለፉት ወራት ያረጋገጣቸው መራራ እውነታዎች የሚከተሉት ናቸው፦
ሆስፒታሉ አገልግሎት ማቋረጡን ተከትሎ የሪፈራል ሥርዓቱ በመናጋቱ የጤና መድህን ተጠቃሚ የነበሩና ወደ ግል ሕክምና መሄድ የማይችሉ ከ3 ሺህ በላይ ምስኪን ዜጎች በየቤታቸውና በየቀበሌያቸው ለሞት ተዳርገዋል።
የደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ጥላሁን ከበደ “ኦቶና ሆስፒታል ታመመ፤ እናክመው!” በሚል መሪ ቃል ጥሪ ካስተላለፉ መጪው ሐምሌ 19 ቀን 2018 ዓ.ም አንድ ዓመት ይሞላዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ ከ5 ወራት በፊት “ግንባታ ሊጀመር ነው” ቢሉም የተቆረጠ ቀን አልገለጹም። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጉቼ ጉሌ ከ4 ወራት በፊት ከገንዘብ ሚኒስቴር “መልካም ቃል” አግኝተናል ቢሉም ዛሬም ግንባታው በተስፋ ቃል ላይ ብቻ ቆሟል።
ከተለያዩ ወገኖች የተሰበሰበው ከፍተኛ ገንዘብና ቁሳቁስ የት እንደደረሰ ለሕዝብ ይፋ ባለመደረጉ በሕዝቡ ዘንድ “ጉዳዩ ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ የዋለ ነበር ወይ?” የሚል ጥርጣሬ ፈጥሯል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየቀረቡ ያሉ አስተያየቶችና ምስጋናዎች እንዳሉ ሆነው፣ ከጋዜጠኝነት ሙያዊ ዕይታና ከተጠያቂነት መርህ አንጻር ሲገመገም፦ ስለወከሉት ሕዝብ መከራ መናገርና መፍትሔ መጠየቅ የሕግና የሞራል ግዴታ እንጂ ለሕዝቡ የሚደረግ “ውለታ” ወይም “ልዩ ስኬት” ሊሆን አይችልም።
አንድ የሕዝብ ተወካይ በምክር ቤት ወንበር ላይ የተቀመጠው የሕዝብን አደራና እምነት ተሸክሞ በመሆኑ የሕዝብን እሮሮ ከፍ አድርጎ ማሰማትና አስፈጻሚውን አካል መሞገት መሠረታዊው ተቋማዊ የሥራ ድርሻው ነው።
እውነተኛ የሕዝብ ውክልና ትርጉም የሚያገኘውም ችግሮችን በምክር ቤት ዘርዝሮ በመተው ብቻ ሳይሆን ለአንገብጋቢ ችግሮች ከመንግሥት አስፈጻሚ አካላት አስቸኳይ መፍትሔና ተግባራዊ እርምጃዎችን በሕግ አግባብ ተከታትሎ ማስፈጸም ሲቻል ነው።
በተወካይ እታፈራው ሞታ የተጀመረው ይህ ጥያቄ በበጎ ጅምርነት የሚወሰድ ቢሆንም በምክር ቤቱ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች የአካባቢው ተወካዮች በተለይም ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፉና አዳዲስ አባላት ይህንን እንደ መነሻ በመውሰድ በንቃት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ ታዛቢዎች ያሳስባሉ።
የኦቶና ሆስፒታል መውደም የሚሊዮኖች የሕይወት ዋስትና መቃጠል በመሆኑ ጉዳዩ በቃላት ጋጋታና በተስፋ ቃላት መራዘም የለበትም። WT Media የሕዝብ ዓይንና ጆሮ በመሆን የተሰበሰበው የሕዝብ ሀብት ኦዲት ተደርጎ የተቆረጠ የግንባታ ቀን ታውቆ መሬት ላይ ተጨባጭ ሥራ እስካልተጀመረ ድረስ ይህንን ሰብዓዊ ቀውስ በቅርበት መከታተሉንና የሕዝብን ድምፅ ማስተጋባቱን አያቆምም።