በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በከፍተኛ ሁኔታ የሚስተዋለው የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ እጥረትና የበጀት ቀውስ መነሻ ምክንያት ምን እንደሆነ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በቅርቡ በዘንድሮ ምርጫ ማግስት የተካሄደና በምስጢር የተቀዳ የድምፅ መረጃ ከታማኝ ምንጮች ለ WT Media ደርሷል።
ይህ የተለቀቀው (leak የተደረገው) የድምፅ መረጃ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ “ለሠራተኞች ደመወዝ የሚሆን የበጀት እጥረት አጋጥሞናል” በማለት ለፌዴራል መንግሥት ላቀረቡት አቤቱታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተሰጠ በማስረጃ የተደገፈ ምላሽ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በድምፅ መረጃው ላይ እንደገለጹት ክልሉ በበጀት እጥረት ሳቢያ ደመወዝ መክፈል አቅቶታል የሚለው መከራከሪያ ከተጨባጩ የፋይናንስ መረጃ ጋር አይገናኝም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንድሮ በሀገሪቱ በተሻሻለው አዲስ የበጀት ቀመር እና የታክስ/የገቢ መጋራት አሠራር ምክንያት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ካለው መደበኛ ዕቅድ ውጭ ብቻውን 1.4 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ገንዘብ ከፌዴራል መንግሥት መውሰዱን ተናግረዋል።
ለሁሉም ክልሎች የሚደረገው ድጋፍና አጠቃላይ በጀት ዘንድሮ ከአምናው ያደገ ሲሆን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጀትም እያደገ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም ሲሉ በዚሁ አፈትልኮ በወጣው ድምፅ ይናገራሉ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፣ የክልሉ እና የዞን ፖለቲካ “ጥቂቶችን ደሞዝተኛ የሚያደርግና አጠቃላይ ሕዝቡን የሚያደኸይ ነው” በማለት በጥብቅ ወቅሰዋል።
ክልሉ ተጨማሪ በጀት እያገኘ ሰራተኛውን መክፈል ያቃተው በከፍተኛ ሙስና እና ከሕግ ውጭ በሆኑ አሠራሮች መሆኑን በሚከተሉት ሁለት አስገራሚ ማስረጃዎች አጋልጠዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርሶ አደሮች ማዳበሪያ ለመግዛት የከፈሉትንና የተሰበሰበውን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የክልሉ አመራሮች ለፌዴራል መንግሥት ሳያስረክቡ አስቀርተውታል ብለዋል።
“ከአርሶ አደሩ በበርካታ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወስደዋል፣ ለኛ ግን አልሰጡም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ፌዴራል መንግሥት ዘንድሮም ማዳበሪያ ለማቅረብ በብድርና በሌላ ድርድር ውስጥ ለመግባት መገደዱን ጠቅሰዋል።
ሌላው እጅግ አስደንጋጭ ማስረጃ፣ ከመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ላይ በየወሩ የሚቆረጠው የጡረታ ዋስትና ገንዘብ፣ ለጡረታ ዋስትና ኤጀንሲ ገቢ አልተደረገም። “ተቆርጧል፣ ግን እዚህ (ኤጀንሲው ጋር) አልገባም” በማለት የሠራተኛው የዕድሜ ልክ ዋስትና ገንዘብ ጭምር የት እንደደረሰ የማይታወቅበት ሌብነት መፈጸሙን አረጋግጠዋል።
ይህ አሁን በጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት በዝርዝር የተጋለጠው የሙስና፣ የሌብነት እና የብልሹ አሠራር ማረጋገጫ፣ WT Media በክልሉ ስላለው ሌብነት፣ የአሰራር ብልሽት፣ የፋይናንስ አስተዳደር መበላሸትና የፕሮጀክቶች መስተጓጎል በተደጋጋሚ ሲጮህበትና ሲዘግብበት የነበረው መራራ እውነታ ነው።
የክልሉ አመራሮች የሕዝብን ጥቅም ለሙስናና ለሌብነት በማዋል በተሰበሰበው ሀብት ላይ ግልጽነትና ተጠያቂነት የለም በሚል የሚዲያችን የምርመራ ቡድን ያወጣቸው ዘገባዎች ሁሉ ዛሬ በቀጥታ ከሀገሪቱ ከፍተኛ ሥልጣን የመነጨ የሰነድና የድምፅ ማስረጃ ተገኝቶላቸዋል።
ሚዲያችን ቀደም ሲል ባደረጋቸው ተከታታይ የምርመራ ዘገባዎች የሚከተሉትን መጠነ-ሰፊ የብዝበዛ ወንጀሎች ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ለአብነትም የጎፋ ዞን የመሬት መንሸራተት አደጋው ለተጎዱ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ ከተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ እርዳታ ሰጪዎች፣ ከቅን ዜጎች ጭምር የተሰበሰበው ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ በአሁኑ ወቅት የት እንደደረሰና ለምን ዓላማ እንደዋለ ሳይታወቅ ጠፍቷል።
በክልሉ በተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ስም የሚመደበው ከፍተኛ የሕዝብ ገንዘብ፣ በአመራሮች እና በጥቅም ተጋሪዎቻቸው መካከል በተዘረጋ ስልታዊ መረብና መመሳጠር በየቀኑ እየተበዘበዘ ይገኛል።
WT Media በዚህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የድምፅ መረጃ ዙሪያ አጭር ሙያዊ አስተያየት እንዲሰጡ የአንድ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምሁርን አነጋግሯል።
እኚሁ ምሁር በክልሉ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ሲያስረዱ ”በአሁኑ ወቅት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየሆነ ያለው ሙስና፣ ሌብነት፣ ዝርፊያ እንዲሁም ብልሹ አሠራር፣ በመሬት ላይ የክልል መንግሥት የለም እስኪባል ድረስ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ማኅበረሰቡ በክልሉ በሚፈጸሙት እነዚህ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች እና በክልሉ ተንሰራፍቶ ባለው የሕጋዊ ተጠያቂነት እጦት ምክንያት በመንግሥት ላይ ፍጹም ተስፋ እየቆረጠ ይገኛል” ብለዋል።
ምሁሩ አክለውም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር አስመልክቶ ሲያብራሩ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ እውነቱን ማውጣታቸውና ችግሩን በግልጽ ማመናቸው መልካም ቢሆንም በተጨባጭ በዚሁ በብልሹ አሠራር እና በሌብነት በተዘፈቁት የአመራር አካላት ላይ ጠንካራ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ በተግባር ማስተካከያ ካላደረጉ ንግግሩ ብቻውን ለሕዝቡ የሚያመጣው ምንም ዓይነት ፋይዳና ጥቅም የለውም” ሲሉ አሳስበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት እና የፋይናንስና ፕላን ልማት ቢሮ፣ ከአርሶ አደሩ የተሰበሰበውና ከሠራተኛው ደመወዝ ላይ የተቀነሰው የጡረታ ገንዘብ የት እንደደረሰ፣ በየደረጃው የተዘረፉ የህዝብ ሀብት እንዲሁም ለጎፋ ተጎጂዎች የተሰበሰበው እርዳታ የት እንደገባ ለሕዝብ አስቸኳይና ይፋዊ ምላሽ ተሰጥቶት ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርበዋል።