በ7ኛው ብሔራዊና ክልላዊ ምርጫ በቁጫ ምርጫ ክልል የተፈጸመውን የተደራጀ የድምፅ ማጭበርበር ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያሳለፈው የውሳኔ ደብዳቤ ከፍተኛ ሕጋዊ ጉድለቶችና የግልጽነት እጥረት ያለበት መሆኑን በመጥቀስ የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) ሙሉ በሙሉ ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቦርዱ ያሰማራው የምርመራ ቡድን በነበረበት ወቅት እውነተኛ የምስክርነት ቃላቸውን በሰጡ ንጹሐን ዜጎች ላይ የአካባቢው የጸጥታ ኃይሎች አሰቃቂ የበቀል እርምጃ፣ ከባድ ድብደባና እስራት እየፈጸሙባቸው መሆኑ ተረጋግጧል።
የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) ዛሬ ሰኔ 09 ቀን 2018 ዓ.ም. ለአባላቱ፣ ለአመራሮቹና ለአጠቃላይ የቁጫ ሕዝብ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ፤ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ተፈርሞ የወጣውንና የፓርቲውን የውጤት መሰረዝ ጥያቄ “በማስረጃ ያልተደገፈ” በሚል ውድቅ ያደረገውን ደብዳቤ በጥልቀት መገምገሙን አስታውቋል።

ፓርቲው “እስካሁን ባለው ያለበቂ ማስረጃ ለቦርዱ ያቀረብነው አንዳችም አቤቱታ የለም” በማለት የቦርዱን ውሳኔ ውድቅ ያደረገ ሲሆን፣ በደብዳቤው ላይ የሕግና የአሠራር ቅቡልነት የሚያሳጡ 2 ታላላቅ ጉድለቶችን በዝርዝር አስቀምጧል።
አንደኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመጨረሻ ውሳኔ ዋና ሰብሳቢዋ (ሜላትወርቅ ኃይሉ) በሥራ ላይ እያሉ በምክትል ሰብሳቢው (ተስፋዬ ንዋይ እንግዳሸት) ተፈርሞ መውጣቱ አግባብ አለመሆኑን፣
በሁለተኛ ደረጃ በቦርዱ የመጨረሻ የውሳኔ ደብዳቤ ላይ የቦርዱ ዋና ማኅተም ማረፍ ሲገባው፣ የ“ፖለቲካ ፓርቲዎች ዘርፍ” ማኅተም ብቻ ማረፉ የሰነዱን ሕጋዊ ቅቡልነት እንደሚያሳጣው ገልጿል።
ቁሕዴፓ አክሎም የቦርዱ ደብዳቤ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ በመሆኑ ጉዳዩን ይበልጥ መርምሮ ተገቢውን ሕጋዊ ምላሽ እንደሚሰጥበት የገለጸ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት በቁጫ ምርጫ ክልል በገዥው ብልፅግና ፓርቲ በኩል “ምርጫውን አሸንፈናል” በሚል እየተደረገ ያለው የሪችት መተኮስና ወከባ ፈጽሞ “ትርጉም አልባ” መሆኑን አስገንዝቧል።
ቦርዱ የላከው የምርመራ ቡድን በአካባቢው በነበረበት ወቅት የምርጫውን ሕገ-ወጥነት ያጋለጡ ምስክሮችን የማጥፋትና የማስፈራራት እርምጃ በአካባቢው የጸጥታ ኃይሎች ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ከአካባቢው ለWT Media የደረሱ ተዓማኒ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በቁጫ አልፋ ወረዳ ለምርጫ ቦርድ የምርመራ ቡድን ቀርቦ እውነተኛ የምስክርነት ቃሉን የሰጠው ወጣት ሕዝቅኤል ፎሻ በአካባቢው የፖሊስ ኃይሎች በደረሰበት አሰቃቂና ጨካኝ ድብደባ ምክንያት በአሁኑ ወቅት በሕይወትና በሞት መካከል ይገኛል።
ከዚህም በተጨማሪ የምርጫውን መጭበርበር አጋልጠዋል የተባሉ 12 ወጣቶች በአስቸኳይ ታስረው የተወሰዱ ሲሆን ከውጭ ዓለም ጋር እንዳይገናኙም የግል የሞባይል ስልኮቻቸው በጸጥታ ኃይሎች ተቀምጧል።
የመብት ጥሰቱ በዚህ ብቻ አላቆመም፤ ትናንት ማታ ከምሽቱ 2:30 ጀምሮ በጮሾ ከተማ ውስጥ በፓትሮል መኪና የተሰማሩ የፖሊስ ኃይሎች፣ ወደ ንጹሐን ዜጎች መኖሪያ ቤቶች በኃይል እየገቡ ሰላማዊ ነዋሪዎችን ክፉኛ ሲደበድቡና ሲያሸብሩ አድረዋል።
WT Media ቀደም ሲል ባወጣቸው ተከታታይ የምርመራ ዘገባዎች እንዳረጋገጠው የቁጫ ብሔረሰብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን መዋቅር ሥር የሚገኝ ቢሆንም ለማንነቱ ዕውቅና ራስን በራስ የማስተዳደር መብትና የራሱ አስተዳደራዊ መዋቅር ተከልክሎ ከፍተኛ መዋቅራዊና አስተዳደራዊ በደል እየደረሰበት ይገኛል።
በ2013 ዓ.ም. በነበረው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ቁሕዴፓ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ አግኝቶ ማሸነፉ የሚታወስ ሲሆን አሁን በተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ግን ገዥው ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳን ከማገድና የፓርቲ ጽሕፈት ቤቶችን በኃይል ከመዝጋት ጀምሮ በዕለተ-ምርጫው የምርጫ አስፈጻሚዎችና የጸጥታ አካላት ከመራጩ ሕዝብ እጅ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን በኃይል በመንጠቅ የተደራጀ የኮሮጆ መነጠቅ ወንጀል መፈጸማቸውን WT Media በስፋት መዘገቡ ይታወሳል።
የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) መላው የቁጫ ምርጫ ክልል ሕዝብ በቀጣይ ከፓርቲው ተጨማሪ መግለጫና ሕጋዊ አቅጣጫ እስኪሰጥ ድረስ ያለአንዳች መረባበሽ ሁሉንም ነገር በትዕግሥትና በሰከነ መንገድ እንዲጠባበቅ ሰላሙን ከምንጊዜውም በላይ እንዲጠብቅ እና የሚደርስበትን ማንኛውንም ችግር ለሚመለከታቸው አካላት እንዲያሳውቅ በአፅንዖት ጥሪ አቅርቧል።
WT Media ከተነሱት አዳዲስ አሰቃቂ የድብደባና የእስራት ክሶች ዙሪያ የአካባቢውን ባለሥልጣናትና የጋሞ ዞን አስተዳደርን ምላሽ ለማካተት በተደጋጋሚ ስልክ ቢደውልም፣ ከሚመለከታቸው አካላት በኩል ስልኮችን ባለማንሳትና ፈቃደኛ አለመሆን የተነሳ ምላሻቸውን ለማግኘት የተደረገው ጥረት አሁንም ሳይሳካ ቀርቷል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በምስክሮች ላይ እየደረሰ ያለውን ሥቃይ አስመልክቶ የሚሰጡትን ምላሽ WT Media በአቅራቢያው ሆኖ መከታተሉን ይቀጥላል።