እነኚህ በዎላይታ ዞን ከ2010 – 2014 ዓ.ም የተመረቁ ሥራ አጥ ወጣቶች ወደ ዞኑ አስተዳደር ቢሮ በሰላማዊ መንገድ በመግባት አመራሮችን ለመጠየቅ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ ተነግሯል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን ውስጥ የሚስተዋለው ስር የሰደደ የሥራ አጥነት ቀውስ አዲስ መልክ እየያዘ መጥቷል።
ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ለዓመታት ሥራ አጥ ሆነው የቆዩ ወጣቶች በዞኑ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሚወጡ የቅጥር ማስታወቂያዎች ላይ እንዳይወዳደሩ ዕገዳና ገደብ እየተጣለባቸው መሆኑን ተከትሎ ከፍተኛ ቅሬታና ቁጭት እየቀሰቀሰ ይገኛል።

ጉዳዩ ያሳሰባቸውና በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የተመረቁ ወጣቶች አስተባባሪዎች ለ WT Media በላኩት መረጃ መሠረት ከ2010 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ የተመረቁ ሥራ አጦች በሙሉ በቅርቡ ቀኑ ተቆርጦ በአንድነት ወደ ዎላይታ ዞን አስተዳደር ቢሮ በመግባት መዋቅራዊ ፍትሕ ለመጠየቅ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውንና ለዚህም ተመራቂዎች እንዲዘጋጁ ጥሪ ማቅረባቸውን አስታውቀዋል።
በዎላይታ ዞን የሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በቅርቡ የሚያወጧቸው የቅጥር ማስታወቂያዎች ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ የተመረቁ አመልካቾችን ብቻ እንዲያመለክቱ የሚገድቡ መስፈርቶችን እያወጡ መሆኑ ወጣቶቹን ክፉኛ አስቆጥቷል።
የተመራቂዎች አስተባባሪዎች ለ WT Media በሰጡት ቃል ”ቀደም ባሉት ዓመታት በመንግሥት በኩል የቅጥር እገዳ ተጥሎ በነበረበት ወቅት ‘ታገሱ’ ተብለን የጠበቅነው ጊዜ ዛሬ በእኛ ላይ እንደ ስህተት ተቆጥሮ ከውድድር ዕድል ውጪ ማድረጊያ መስፈርት መሆኑ ፍጹም ፍትሐዊ አይደለም። ይህ አድሎአዊ የመመሪያ አተገባበር በአስቸኳይ ሊታረም ይገባል” ብለዋል።
በትምህርታቸው ላይ ዓመታትን ያጠፉ ቤተሰቦቻቸውም ብዙ ወጪ ያወጡባቸው እነዚህ ወጣቶች አሁን ላይ የቅጥር ሂደቱ በምረቃ ዓመት ብቻ ገደብ ሲያደርግ ተስፋ ወደ መቁረጥ መድረሳቸውን ይገልጻሉ።
ከተመራቂዎቹ ዘንድ የሚሰሙ ድምፆች እንደሚያመለክቱት ቀደም ሲልም የነበሩት ጥቂት ቅጥሮች በዘመድ በጎሳና በጥቅም ትስስር (ሙስና) የሚፈጸሙ በመሆናቸው ለዓመታት ዕድሉ ተነፍገው የቆዩ ሲሆን አሁን ደግሞ ጭራሽ በሕጋዊ መንገድ እንዳይወዳደሩ መታገዳቸውን “መዋቅራዊ በደል” ሲሉ ይጠሩታል።
በቅርቡ የተካሄዱ መሬት ላይ ያሉ የተለያዩ የዳሰሳ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በዎላይታ ዞን ብቻ ከዲግሪና ከዚያ በላይ የተማሩ ከ200 ሺህ በላይ ሥራ አጥ ወጣቶች ይገኛሉ።
ይህ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ሊመዘገብ የቻለው በአካባቢው መዋቅራዊ የሥራ ዕድል ፈጠራ ባለመኖሩና የተማረው የሰው ኃይል በተለያዩ ሙያዎች ሰልጥኖ ለበርካታ ዓመታት ቤት ለመቀመጥ በመገደዱ እንደሆነ ጥናቶቹ ያሳያሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ WT Media በቅርቡ ይፋ ባደረጋቸው የምርመራ ዘገባዎች መሠረት፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ከፌዴራል መንግሥት ከተመደበው መደበኛ በጀት ውጭ ብቻውን በቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ያገኙ ቢሆንም ገንዘቡ ለሕዝብ አገልግሎትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ከመዋል ይልቅ የአርሶ አደሩ የማዳበሪያ ገንዘብ እና የሠራተኛው የጡረታ ዋስትና ሳይቀር በአመራሮችና በጥቅም ተጋሪዎቻቸው ስልታዊ መረብ እየተበዘበዘ መሆኑን ጭምር መጋለጡ ይታወሳል።

እንዲሁም በርካታ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ስም የወጡ ገንዘቦች የት እንደደረሰ በማይታወቅበት እና የክልሉና የዞኑ ፖለቲካ “ጥቂቶችን ብቻ ደሞዝተኛ በሚያደርግበት” በዚህ አስከፊ የሙስና ስብጥር ውስጥ የወጣቱ የሥራ እጦት ጥያቄ ተገቢውን ተቋማዊ ምላሽ አላገኘም የሚለው የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ትንተናም የዚሁ ቀውስ ማሳያ ነው።
”ፍትሕ ለ2010-2014 ተመራቂዎች!” በሚል መሪ ቃል የተደራጁት ወጣቶች የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች ይህንን አግላይ አሠራር በአስቸኳይ እንዲያስተካክሉና ለሁሉም ብቁ ምሩቃን እኩል ዕድል የሚሰጥ አካታችና ፍትሐዊ የቅጥር ሥርዓት እንዲዘረጉ በጥብቅ እየጠየቁ ይገኛሉ።
ወደ ዞኑ አስተዳደር ቢሮ በጋራ የሚገቡበትን የተወሰነ ቀን በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርጉ ያስታወቁት አስተባባሪዎች ሁሉም ተጎጂ ምሩቃን መብቱን ለማስከበር ዝግጁ እንዲሆን አሳስበዋል።
WT Media በጉዳዩ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው ያልተሳካ ቢሆንም የወጣቶችን ሕጋዊ የሥራ ዕድል ጥያቄ እና የዞኑ አስተዳደር የሚሰጠውን ምላሽ በቅርበት እየተከታተለ መረጃዎችን ማቅረቡን ይቀጥላል።