GridArt_20260611_155735788

በቁጫ የምርጫ ማጭበርበርን ለማጣራት ለምርጫ ቦርድ የምስክርነት ቃል በሰጡ ዜጎች ላይ የበቀል እርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ተገልጿል።

​ በ7ኛው ብሔራዊና ክልላዊ ምርጫ በቁጫ ምርጫ ክልል ተፈጽመዋል የተባሉ መጠነ-ሰፊ የምርጫ ሕግ ጥሰቶችና የድምፅ ማጭበርበር ውንጀላዎችን ለማጣራት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰማራው የምርመራ ቡድን ሥራ መጀመሩን ተከትሎ፣ ለቡድኑ መረጃና የምስክርነት ቃል በሰጡ ንጹሐን ዜጎች ላይ የአካባቢው የጸጥታ ኃይሎች አሰቃቂ የበቀል እርምጃ፣ ድብደባና እስራት እየፈጸሙባቸው መሆኑን ከስፍራው ለ WT Media የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

​ከአካባቢው ለ WT Media የደረሱ ተዓማኒ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በቁጫ አልፋ ወረዳ ለምርጫ ቦርድ የምርመራ ቡድን ቀርቦ እውነተኛ የምስክርነት ቃሉን የሰጠው ወጣት ሕዝቅኤል ፎሻ በአካባቢው የፖሊስ ኃይሎች ክፉኛ ተደብድቦ በአሁኑ ወቅት በሞት አፋፍ ላይ ይገኛል።

​ከዚህም በተጨማሪ የምርጫውን መጭበርበር አጋልጠዋል የተባሉ 12 ወጣቶች በአስቸኳይ ታስረው የተወሰዱ ሲሆን ከውጭ ዓለም ጋር እንዳይገናኙም የግል የሞባይል ስልኮቻቸው በጸጥታ ኃይሎች ተቀምጧል።

​የመብት ጥሰቱ በዚህ ብቻ አላቆመም፤ ትናንት ማታ ከምሽቱ 2:30 ጀምሮ በጮሾ ከተማ ውስጥ በፓትሮል መኪና የተሰማሩ የፖሊስ ኃይሎች ወደ ንጹሐን ዜጎች መኖሪያ ቤቶች በኃይል እየገቡ ነዋሪዎችን ያለምንም አንዳች ጥፋት ክፉኛ ሲደበድቡና ሲያሸብሩ አድረዋል።
​
​WT Media ቀደም ሲል ባወጣቸው ተከታታይ ዘገባዎች እንዳረጋገጠው፣ የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በምርጫ ክልሎቹ የተካሄደውን የ7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ውጤት ሙሉ በሙሉ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።

ፓርቲው በዕለተ-ምርጫው የምርጫ አስፈጻሚዎች የገዥው ብልፅግና ፓርቲ ታዛቢዎች እና የጸጥታ አካላት ከመራጩ ሕዝብ እጅ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን በኃይል ሲቀሙ ውለዋል በሚል የ“ኮሮጆ መነጠቅ” ክስ አቅርቦ ነበር።

ቁሕዴፓን የመረጡ ዜጎችን ስም ዝርዝር ለጸጥታ አካላት አሳልፎ የመስጠት እና መራጮችን የማስፈራራት ድርጊቶች መፈጸማቸውንም ገልጿል።

​የቁጫ ብሔረሰብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን መዋቅር ሥር የሚገኝ ቢሆንም፣ ለማንነቱ ዕውቅና፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትና የራሱ አስተዳደራዊ መዋቅር ተከልክሎ ከፍተኛ መዋቅራዊ በደል እየደረሰበት እንደሚገኝ WT Media በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።

በ2013 ዓ.ም. በነበረው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ቁሕዴፓ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ አግኝቶ ማሸነፉ የሚታወስ ሲሆን አሁን በተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ግን ገዥው ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳን ከማገድና የፓርቲ ጽሕፈት ቤቶችን በኃይል ከመዝጋት ጀምሮ ሰፊ የድምፅ ማጭበርበር እንደፈጸመ ፓርቲው በጥብቅ ኮንኗል። 

​የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ የቁሕዴፓ አቤቱታ በጽሑፍ እንደደረሳቸውና የሕግ ክፍላቸው ጉዳዩን መርምሮ የቀጣይ ማጣራት ሥራ እንደሚሠራ በይፋዊ መግለጫቸው ማረጋገጣቸው ይታወሳል።

ቁሕዴፓ የተፈጸሙት የሥነ-ምግባር ጥሰቶች በጣት አሻራ ምርመራ የሚረጋገጡ በመሆናቸው በምርጫ ጣቢያዎች ላይ የፎረንሲክ ምርመራ እንዲደረግ ለቦርዱ በጽሁፍ ማመልከቱን ገልጾ ነበር።

​ነገር ግን ቦርዱ የላከው የምርመራ ቡድን በአካባቢው ሥራ በጀመረበት በዚህ ወቅት የምርመራ ሂደቱን ለማደናቀፍና እውነቱ እንዳይወጣ ለማድረግ ምስክሮችን የማጥፋት፣ የማስፈራራትና በኃይል የመደብደብ እርምጃ መወሰዱ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል።

​WT Media ከተነሱት አዳዲስ አሰቃቂ የድብደባና የእስራት ክሶች ዙሪያ የአካባቢውን ባለሥልጣናት፣ የጋሞ ዞን አስተዳደርን እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ምላሽና አስተያየት ለማካተት በተደጋጋሚ ስልክ ቢደውልም ከሚመለከታቸው አካላት በኩል ስልኮችን ባለማንሳትና ፈቃደኛ አለመሆን የተነሳ ምላሻቸውን ለማግኘት የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media