በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን፦ በአርባ ምንጭ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በባለቤቱ እህት ላይ አስጸያፊ የግብረ ሥጋ ድፍረት ወንጀል የፈጸመውን ተከሳሽ በ20 ዓመት ጽኑ እስራት መቅጣቱን አስታውቋል።
የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ መምሪያ የሴቶችና ሕፃናት ልዩ የምርመራና ክስ የሥራ ሒደት የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ጥፋተኛ የተባለው ግለሰብ አቶ ኃይማኖት ዮሐንስ ይባላል።
ተከሳሹ እሁድ ዕለት መጋቢት 13 ቀን 2018 ዓ.ም ሌሊት፣ በሼቻ ክፍለ ከተማ ዶይሳ ቀበሌ አሻም ሆቴል ጀርባ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ውስጥ ነው ወንጀሉን የፈጸመው።
በወቅቱ ባለቤቱ ለሥራ ጉዳይ ከአገር ቤት ውጪ መሆኗን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከእነሱ ጋር በአንድ ቤት ውስጥ በሥራ አጋዥነት የምትኖረውን የ12 ዓመት ታዳጊ የባለቤቱን እህት (ለዘገባው ስሟ የተቀየረ-ንጋቷ ተረፈን) ኢ-ሰብዓዊ ጥቃት ሰለባ አድርጓታል።
የዓቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያመለክተው ተከሳሹ በመጀመሪያ በቤት ውስጥ ባለው ቴሌቪዥን ላይ የወሲብ (ፖርኖግራፊ) ፊልም እንድትመለከት ካደረገ በኋላ የለበሰችውን ልብስ በጉልበት አውልቆ በመራቢያ አካሏና በመቀመጫዋ ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጽሞባታል።
ድርጊቱንም ለሰዎች እንዳትናገር በጥብቅ ያስጠነቀቃት ቢሆንም በደረሰባት ከባድ የአካልና የሥነ-ልቦና ሕመም ምክንያት ታዳጊዋ ጉዳዩን ለጎረቤት በመናገሯ የወንጀል ምርመራው ሊጀመር ችሏል።
የአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳዮች ልዩ መርማሪ ከዓቃቤ ሕግ ጋር በመቀናጀት የምርመራ መዝገቡን በሰውና በሰነድ (በሕክምና) ማስረጃዎች አስደግፎ ለፍርድ ቤት አቅርቧል።
ዓቃቤ ሕግም በተከሳሹ ላይ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 627(4)(ሀ) መሠረት በሕፃናት ላይ የሚፈጸም የግብረ ሥጋ ድፍረት ወንጀል ክስ መስርቶበታል።
ጉዳዩን የተመለከተው የአርባ ምንጭ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሕፃናት ልዩ ችሎት የቀረቡትን ακሙራና ጠንካራ ማስረጃዎች መርምሮ ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን ሰጥቶ ነበር።
ተከሳሹ የመከላከያ ማስረጃዎችን ቢያቀርብም የዓቃቤ ሕግን ያደቀቀ ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ በጥፋተኝነት ወስኖበታል።
በዚህም መሠረት በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በወጣው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 3/2017 መሠረት የወንጀሉን ደረጃ 5 የእስራት ቅጣት እርከን 42 ላይ በማሳረፍ ተከሳሹን ያርማል ሌሎችንም ያስተምራል በሚል በ20 (ሃያ) ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ በፍርድ ቤቱ ተወስኗል።
የግል ተበዳይ ታዳጊዋ ቤተሰቦች ከውሳኔው በኋላ ለ WT Media በሰጡት አጭር አስተያየት፤ የተላለፈው የ20 ዓመት ጽኑ እስራት ፍርድ የተደፈረውንና የተሰበረውን የታዳጊዋን ሥነ-ልቦና ሙሉ በሙሉ ሊያክም ባይችልም በማኅበረሰቡ ውስጥ መሰል አስጸያፊ ድርጊቶችን ለመግታትና ሌሎች መሰል ወንጀለኞች እንዲማሩበት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።