WT Media ያጠናቀረው ልዩ የምርመራ ዘገባ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን መዋቅር ሥር በሚገኙ የዘይሴ እና የቁጫ ብሔረሰብ ተወላጆች ላይ የመንግሥትን የጸጥታ ኃይሎች ያካተተ ከባድ የመብት ጥሰት፣ ግድያ፣ መፈናቀል፣ ንብረት ማውደም እና ሕገ-ወጥ እስራት እየተፈጸመባቸው መሆኑን ከአካባቢው ነዋሪዎችና ከተጎጂዎች ለ WT Media የደረሱ ታማኝ የመረጃ ምንጮች በዝርዝር ገልጸዋል።
ጥቃቱ በተለይ ከ7ኛው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ውጤት መታወቅ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰጣቸውን ይፋዊ ውሳኔዎች ተከትሎ ይበልጥ አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሱ ታውቋል።
የዘይሴ ብሔረሰብ አባላት ከአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከበር ግንባር ቀደም በመሆን ታላቅ መስዋዕትነት የከፈሉ ሕዝቦች ቢሆኑም በአሁኑ ወቅት ግን በክልሉ መዋቅር ከፍተኛ በደል እየደረሰባቸው ይገኛል።
ከአካባቢው የደረሱ ታማኝ የመረጃ ምንጮች እንደሚያሳዩት ይህ ጥቃት በተለይ ከሰኔ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ጥቃቱ ሊሰነዘር የቻለው የዘይሴ ሕዝብ በሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት መሠረት ያቀረበውን «ራስን በራስ የማስተዳደር፥ የልዩ ወረዳ ወይም የዞን መዋቅር ይፈቀድልን» የሚለውን ጥያቄ ተከትሎ ነው።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ አመራር “የዘይሴ ሕዝብ ራሱን ችሎ ከጋሞ ዞን ሥር ለምን ይወጣል?” የሚሉ የሐሰት ትረካዎችን በመፍጠር ሕዝባዊ ጥያቄውን በኃይል ለማፈን በወሰዱት እርምጃ ሳቢያ ጥቃቱ ሊቀሰቀስ ችሏል።
በአሁኑ ሰዓት በክልሉ የጸጥታ አካላት (በተለይም በአድማ ብተና)፣ በጋሞ ዞን መደበኛ ፖሊስ እና በበጋሞ ዞን ቀድሞው የልዩ ኃይል አባላት አማካኝነት በጋርዛታ በኩል በልዩ ስሙ “ሻንካ” እና “ዳምብሌ ሰው” በሚባሉ አካባቢዎች በዘይሴ ማኅበረሰብ ላይ መጠነ-ሰፊ ጥቃትና ጅምላ ጭፍጨፋ እየተፈጸመ ይገኛል።
በዚህ ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ የነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ በእሳት እንዲጋዩ ተደርገዋል። የአካባቢው አርሶ አደሮች የለፉበት ጤፍ ከነክምሩ በቆሎ ከነጎተራው፣ ማሽላና ሌሎች ሰብሎች በመንግሥታዊ የጸጥታ መዋቅር ስም በተደራጁ አካላት ሆን ተብሎ ተቃጥሏል።



በርካታ ንጹሐን ዜጎች ሕይወታቸውን ለማዳን በአካባቢው በሚገኙ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖችና የሙዝ ተክሎች ሥር ተሸሽገውና ተሰደው እንደሚገኙ ለጣቢያችን በሃዘን ገልጸዋል።
ይህ መጠነ-ሰፊ ጥቃት የተከፈተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 10 ቀን 2018 ዓ.ም በቁጥር አ1162/11/841 በወጣው ይፋዊ ደብዳቤ መሠረት የጋሞ ዞን እና የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ በዘይሴ ልዩ ምርጫ ክልል ላይ አቅርቦት የነበረውን የ”ምርጫ ሕግ ጥሰት” ክስ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ ነው።
ቦርዱ ያሰማራው አጣሪ ኮሚቴ የብልፅግና ክስ በቂ ማስረጃ የሌለው መሆኑን በማረጋገጡ በምርጫው ሰፊ የሕዝብ ድምፅ ያገኘው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ ተፎካካሪዎች ማሸነፋቸው በይፋ ተረጋግጧል።
በዚህ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) በድጋሚ የተመረጡት አቶ አብርሃም አሞሼ ከዚህ ቀደም ለWT Media በሰጡት ልዩ ቃለ-መጠየቅ በዕለተ-ምርጫው በዘይሴ ዳምብሌ፣ ኤልጎ እና ፋንጎ ጣቢያዎች ላይ የብልፅግና ቀበሌና ወረዳ አመራሮች መራጮችን በጥፊና በዱላ እየደበደቡ ከሰልፍ ሲያባርሩ እንደነበር ማስታወሳቸው ይታወሳል።



አቶ አብርሃም መዋቅሩ የዘይሴን ሕዝብ ከራሱ መልክዓ-ምድር አጥፍቶ መሬቱን ለመውረስና ለራሱ ወገን ለማስፈር የተደራጀ የዘር ማጥፋት ዕቅድ እንዳለውና የሕዝቡ ድምፅ የመዋቅር ጥያቄው እንዲመለስለት ለመንግሥት ያስተላለፈው መልእክት መሆኑን ገልጸው ነበር።
በዚሁ የጋሞ ዞን መዋቅር ውስጥ ሌላው ከፍተኛ በደልና ጫና እየደረሰበት የሚገኘው የቁጫ ብሔረሰብ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለWT Media ተናግረዋል።
በቁጫ ምርጫ ክልል በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተፈጸመውን የተደራጀ የኮሮጆ መነጠቅና ማጭበርበር ተከትሎ የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) ያቀረበውን አቤቱታ ለማጣራት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕግ አጣሪ ኮሚቴ ማሰማራቱ ይታወቃል።
ነገር ግን ለዚህ የአጣሪ ኮሚቴ እውነተኛ የምስክርነት ቃል እና መረጃ የሰጡ ንጹሐን ዜጎች ላይ በአሁኑ ሰዓት ከባድ ድብደባ፣ ማሰቃየትና እስራት እየተፈጸመባቸው ነው።
የቀበሌ አመራሮችና ታጣቂ ሚሊሻዎች በመቀናጀት ሰዎችን እያደኑ እያሰሩ የሚገኝ ሲሆን ከትናንት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በሞጎላ ደረቅ ጣቢያ ብቻ ከ20 በላይ ንጹሐን ግለሰቦች ታስረው በከባድ ድብደባና እስራት እየተሰቃዩ መሆኑ ተረጋግጧል።
ይህም ቀደም ሲል በቁጫ አልፋ ወረዳ የምስክርነት ቃል የሰጠው ወጣት ሕዝቅኤል ፎሻ በፖሊስ ተደብድቦ በሞት አፋፍ ላይ ከሚገኝበት እና በጮሾ ከተማ ፖሊሶች በምሽት ወደ ሰው ቤት እየገቡ ነዋሪዎችን ሲደበድቡ ካደሩበት አሰቃቂ ድርጊት ጋር የተያያዘ መሆኑ ታውቋል።
WT Media ቀደም ሲል ከቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባደረገው ልዩ ቃለ-መጠየቅ እና ፓርቲው በይፋ ባወጣው መግለጫ ላይ እንደተመለከተው፤ በቁጫ ምርጫ ክልል ገዥው ፓርቲ የሕዝብን ድምፅ በኃይል ለመቀማት ያደረገውን ሕገ-ወጥ የኮሮጆ አፈና ፓርቲው በማስረጃ አስደግፎ ለምርጫ ቦርድ ማቅረቡ ይታወሳል።
የፓርቲው አመራር በወቅቱ ለጣቢያችን በሰጡት ቃል የቁጫ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እና የዞን መዋቅር ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ማቅረቡን ተከትሎ የመንግሥት የጸጥታ መዋቅር በአመራሮችና በደጋፊዎች ላይ ያነጣጠረ ስልታዊ አፈና እና እስራት ሲያካሂድ መቆየቱን በዝርዝር አጋልጠው ነበር።
ቁሕዴፓ በቅርቡ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ አጣሪ ኮሚቴው በቦታው ተገኝቶ እውነታውን በሚመረምርበት ወቅት መዋቅሩ ምስክሮችን በማስፈራራትና በማሰር እውነት እንዳይወጣ ለማድረግ እየጣረ መሆኑን በጥብቅ አውግዟል።
አሁንም በሞጎላ ደረቅ ጣቢያ የታሰሩት ወገኖች በአስቸኳይ እንዲፈቱና በሕዝቡ ላይ የሚደረገው የበቀል እርምጃ እንዲቆም ፓርቲው በመግለጫው ጠይቋል።
WT Media ቀደም ሲል ባወጣቸው ተከታታይ የምርመራ ዘገባዎች እንዳረጋገጠው የቁጫ እና የዘይሴ ብሔረሰቦች ለማንነታቸው ዕውቅና፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትና የራሳቸው መዋቅር ተከልክለው በጋሞ ዞን ሥር ከፍተኛ መዋቅራዊ በደል እየደረሰባቸው ይገኛል።
በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት የሰጡ ምሁራን እንደሚናገሩት ንጹሐን ዜጎች ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን በመጠየቃቸው ወይም ለሕጋዊ አካል ምስክርነት በመስጠታቸው ብቻ የሚፈጸምባቸው ማንኛውም ድብደባ፣ ማፈናቀል፣ ጅምላ ጭፍጨፋና ሕገ-ወጥ እስራት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና ዓለም አቀፍ ወንጀል ነው። ሰው በተወለደበት አካባቢ በሰላም ወጥቶ መግባት መሠረታዊ መብቱ ነው ይላሉ።
WT Media የሚዲያ ሥነ-ምግባርን በተከተለ መልኩ በተደጋጋሚ በቁጫ እና በዘይሴ ብሔረሰቦች ላይ እየደረሰ ያለውን መጠነ-ሰፊ ጥቃት በተመለከተ ምላሽና ማብራሪያ ለማግኘት የአካባቢውን ባለሥልጣናት፣ የጋሞ ዞን አስተዳደርን እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን በስልክ ለማግኘት ተከታታይ ጥረት ቢያደርግም፣ ስልኮችን ባለማንሳትና ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ለጊዜው ሳይሳካ ቀርቷል።
የፌደራል መንግሥት፣ ሚዲያዎች፣ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ግለሰቦች እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጉዳዩን በትኩረት እንዲያዩት፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበር እና የማኅበረሰቡ ሰላምና ደኅንነት በአስቸኳይ እንዲጠበቅ WT Media ድምፁን በድጋሚ ያሰማል። እንደወትሮው ሁሉ ሁኔታዎችን በቅርበት መከታተላችንን እንቀጥላለን።
1 thought on “በጋሞ ዞን መዋቅር ሥር በሚገኙ በዘይሴና በቁጫ ብሔረሰቦች ላይ ያነጣጠረ መዋቅራዊ ጥቃት፣ ጅምላ ጭፍጨፋና እስራት እየተፈጸመ መሆኑን ነዋሪዎችና የህዝብ ተወካዮች ተናገሩ”
Comments are closed.