በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዎላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞኑ የፋይናንስ ኃላፊዎች እና ያለ ጨረታ ሥራውን ከተረከቡ ኮንትራክተሮች ጋር በመመሳጠር የሕዝብና የመንግሥትን በጀት ለመቀራመት ከፍተኛ የሆነ የሙስና እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ WT Media አረጋግጧል።
ከውስጥ ምንጮች ለWT Media የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ለዚህ ከፍተኛ የበጀት ማጭበርበር እና ምዝበራ ዋነኛው ማሳያ የሆነው የዞኑ አስተዳደር ሕንጻ እድሳት ጉዳይ ነው።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ ይህንን የዕድሳት ምክንያት በማድረግ ቢሮ መግባት ካቆሙ አሁን በትክክል 2 ወራት አስቆጥረዋል።
የሕንጻውን ግንባታ ሂደት በቅርበት የሚያውቁ ወገኖች እንደገለጹት በጥቅሉ ሕንጻው ሲገነባ የፈጀው ጠቅላላ ወጪ 80 ሚሊዮን ብር ብቻ ነበር። ነገር ግን አሁን ላይ የዞኑ የፋይናንስ መዋቅር ለሕንጻው የውስጥና የውጭ ቀለም ለመቀባት እንዲሁም የመብራት አምፖሎችን ለመቀየር ብቻ እጅግ አስደንጋጭ የሆነ 200 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጎ ወደ ሥራ ገብቷል።
በዚህ “ዕድሳት” ሰበብ በአሁኑ ወቅት በሕንጻው ውስጥ የሚገኙ ከ10 በላይ የሚሆኑ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሥራቸው ተቋርጦ ለሕዝብ የሚሰጡት መደበኛ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ቆሞ ይገኛል።
ይህ 200 ሚሊዮን ብር ለቀለም ቅብ በባከነበት በዎላይታ ዞን ውስጥ ከ200 ሺህ በላይ የተማሩና የሥራ ዕድል ያጡ ወጣቶች አማራጭ አጥተው የሚማቅቁበት፣ አጠቃላይ ሕዝቡ መሠረታዊ በሆኑ የልማት አቅርቦቶች ተጠምቶ ባለበት እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞች መደበኛ ወርሃዊ ደመወዛቸው በወቅቱ የማይከፈልበት ተጨባጭ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በተደጋጋሚ የዘገብነውን መረጃ ያረጋግጣል።
እንዲህ ባለ ከባድ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ባለ ዞን 200 ሚሊዮን ብር ለአንድ ሕንጻ ቀለም መቀቢያ ማፍሰስ ምን ያህል የሕዝብን ሕይወት መናቅና የራስን ጥቅም ማሳደድ እንደሆነ መገመት አያቅትም ሲሉ ነዋሪዎችና ታዛቢዎች በምሬት ይናገራሉ።
WT Media የደረሰውን ይህንን ተጨባጭ መረጃ መነሻ በማድረግ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ከዞኑ የፋይናንስ ኃላፊዎች እና ከከፍተኛ የአስተዳደር አካላት ፊት ለፊት ምላሽ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም አመራሮቹ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እስካሁን የተሳካ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም።
የWT Media የምርመራ ክፍል ጉዳዩን በቅርበት መከታተሉን የሚቀጥል ሲሆን ከዞኑ ፋይናንስና ከአስተዳደሩ የሚሰጡ ማብራሪያዎች ካሉ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ይገልጻል።