በዛሬው ዕለት በማለትም ቅዳሜ ዕለት ሰኔ 22 2018 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአርባ ምንጭ ከተማ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን አስመልክተው ያደረጉት ንግግር፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ 12 ዞኖች እና ከ32 በላይ በሚሆኑ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣንና የፍትሐዊነት ጥያቄን አስነስቷል።

ደቡብ ኢትዮጵያ የአንድ ዞን ወይም የአንድ ከተማ ብቻ ክልል አለመሆኑን የሚያነሱት ነዋሪዎቹ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የክልሉን ሰፊ ብዝኃነት ወደ ጎን በመተው ለአንድ አካባቢ ብቻ የሰጡት የተለየ ትኩረትና ያሳዩት አድልዎ በበርካቶች ዘንድ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ተቃውሟቸውንና ቅሬታቸውን የገለጹ የሳውላ፣ የዲላ እና የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ስለተፈጠረው መዋቅራዊ መገለልና የሕብረተሰቡ እሮሮ በተመለከተ ለ WT Media ሀሳባቸውን አካፍለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአርባ ምንጭ ከተማ የተሠሩ ሥራዎችን በሚረቁበት ወቅት “በጣም የሚያሳስበኝና የሚያስፈራኝ ነገር ጥቂት ሠርተን በጣም የምንረካው ነገር ነው፤ እርካታ አደገኛ በሽታ ነው!” ማለታቸው ይታወሳል።
አሁን የተሠራው አርባ ምንጭ ከሚገባት የተፈጥሮ ጸጋና አቅም አንጻር ገና 1 በመቶ (1%) ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ላይ የክልሉን ብሔረሰቦች መደጋገፍ አስመልክተው የሚከተለውን ብለዋል፦
“ኮንሶ ከጋሞ አያንስም፤ ዳሰነች ከዎላይታ አያንስም። ሁሉም ሕዝብ እኩል ነው። እኔ እበልጣለሁ የሚል ስሜት እኔ እሻላለሁ የሚል ስሜት፣ ካለኔ አንደኛ የለም የሚል ስሜት ለዘመናት ደሃ አድርጎ አቆይቶናል። …ከማንኛውም በላይ በችግር በመከራ አብሮ የኖረ ሕዝብ፣ መተባበርና በአርባ ምንጩ ለውጥ ሶዶ መሳቅ ካልቻለ፣ በሶዶ ለውጥ ጂንካው መሳቅ ካልቻለ ሌላው ሰውማ እንዴት ደስ ሊለው ይችላል?” ብለዋል።
ይሁን እንጂ ይህ ንግግር የክልሉ 12 ዞኖችና 32 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ የገነቡትንና የሚጋሩትን ክልል ፍትሐዊነት ያላገናዘበ፣ ይልቁንም ሀብት በአንድ ቦታ ላይ እየተከመረ በጀት ለታጣላቸው ሌሎች አካባቢዎች “በአርባ ምንጭ ለውጥ ሶዶ መሳቅ አለበት” የሚል የተዛባ እይታን ያነጸባረቀ ነው በሚል በምሁራኑ ዘንድ ከፍተኛ ትችን እያስተናገደ ይገኛል።
የWT Media የምርመራ ክፍል በተደጋጋሚ በሰነድና በማስረጃ አስደግፎይፋ እንዳደረገው፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሪዎች የክልሉን ሰፊ ሀብትና በጀት በፍትሐዊነት ለ32ቱም ብሔረሰቦች ከማማረር ይልቅ መዋቅራዊ በሆነ መንገድ ወደ አንድ አካባቢ ብቻ እያፈሰሱት ይገኛል።
የምሁራኑና የነዋሪዎቹ ቁጣ መነሻ የሆኑት ተጨባጭ የልማት በደሎች መካከል በባስኬቶ ዞን ንጹሕ መጠጥ ውኃና መብራት ሙሉ በሙሉ በጠፋበት፣ በኮንሶና ቡርጂ ዞኖች መሠረታዊ ድልድይ ባለመኖሩ ሕዝብ ወንዝ መሻገር አቅቶት በመንገድ ላይ ሕይወቱ በሚያልፍበት፣ በኮሬና ጋርዱላ እናቶች በምጥ ምክንያት መንገድ ላይ እየሞቱ ባሉበት፣ እንዲሁም በጎፋ (ሳውላ)፣ ጌዴኦ (ዲላ) እና ዎላይታ ለዓመታት የተጀመሩ ኮር (Core) የሆኑ የመንገድና የውኃ ፕሮጀክቶች በበጀት እጥረት ቆመው እያለ፤ የክልሉን ሀብት በአንድ ከተማ ላይ ብቻ ከምሮ “የአፍሪካ ምሳሌ” ለማድረግ መሞከር በ32ቱም ብሔረሰቦች ላይ የተፈጸመ “ግልጽ የልማት አድልዎ ነው ነው” በሚል አስረድተዋል።
ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጋሞ ዞን ቦረዳ ወረዳ የጎበኙት የ‘ዮ ሆልዲንግ’ የድንጋይ ከሰል ፋብሪካ፤ የሕዝብና የሀገር ሀብት ለጥቂት አመራሮች ጥቅምና ስርቆት መዋሉን ያሳየ ነው። የ‘ማራ ማይነርስ’ ባለቤት ኢንጂነር ብርሃነመስቀል ክንፈ በ2015 ዓ.ም ያቀረበውንና በአቶ ብርሃኑ ዘውዴ የተሰረከውን የፈጠራ ሐሳብ መነሻ በማድረግ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ የገዛ ቤተሰቦቻቸውን በአባልነት ያቀፉበትን “ዮ ሆልዲንግ” PLC በምስጢር አቋቁመዋል።
መብቱን የጠየቀውንና ይህንን የማዕድን ሌብነት የታገገውን ኢንጂነር ብርሃነመስቀልን በሐሰተኛ የወንጀል ክስ ላለፉት 11 ወራት በማረሚያ ቤት አሳስረውት ይገኛሉ።
እንደ ዎላይታ ሶዶ ያሉ ከተሞችና ዞኖች በጥቅሉ ከ8.15 ቢሊዮን ብር በላይ ግብር በመክፈል የክልሉ ዋነኛ የምጣኔ-ሀብት ደጋፊ እየሆኑ፣ በአንጻሩ ግን እንደ ባለሀብት በረከት አደራ እና አቶ ዳኜ ዳባ ያሉ ጥቅመኞች የሕዝብን ለም መሬት ይዘው ለዓመታት ግብር ሳይከፍሉ፣ መሬቱን ለባንክ አስይዘው የቢሊዮን ብር ብድር በመውሰድ አካባቢውን ጥላ የመጥፋት ግልጽ ወንጀል ፈጽመዋል።
በክልሉ የሚመነጨው ግብር ለሁሉም 12 ዞኖች ልማት መዋል ሲገባው ለአንድ አካባቢ ብቻ መፍሰሱ የምሁራኑና የነዋሪዎቹ ዋነኛ መከራከሪያ ነው።
የሦስቱ መነሻ ከተሞች ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ሰላማዊ ሕባብና የልማት ጥያቄ በሚከተሉት የጋራ ነጥቦች ላይ በመቆም ያስረዳሉ።
በክልሉ ውስጥ የሚገኙት 32ቱም ብሔር ብሔረሰቦች (ኮንሶ፣ ዳሰነች፣ ጋሞ፣ ዎላይታ፣ ጎፋ፣ ጌዴኦ እና ሌሎችም) የየራሳቸው ታሪካዊ መነሻና ክብር ያላቸው በመሆኑ፣ ማናቸውም ዓይነት “እኔ እበልጣለሁ” ወይም “የበላይ ነኝ” የሚሉ ስሜቶች ሳይኖሩ የጋራ ጥቅማቸው ሊከበር ይገባል።
የትኛውም ዞን ከሌላው ሳይበልጥና ሳያንስ የመንግሥት የአስተዳደርና የሀብት ክፍፍል መዋቅር ሆን ተብሎ ለአንድ ወገን ብቻ ጥቅምን በሚሰጥ መልኩ መዘርጋት የለበትም በሚል ምሁራን ያስረዳሉ።
አሁን ላይ ያለው አካሄድ እንደ ዎላይታ፣ ሳውላ እና ዲላ ያሉ ከተሞች ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር፣ የተማረ የሥራ አጥ ወጣት እና የልማት ጥማት ያለባቸው በመሆናቸው፤ ከተሞቹን ማሳደግና ተገቢውን የበጀት ድርሻ መስጠት የክልሉ ህልውና ጥያቄ ነው።
በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች ለዘመናት አብረው በሰላም የኖሩና ዛሬም ሰላማዊ የሆኑ፥ ጥያቄያቸውም “ለእገሌ ብሔር ወይም ከተማ ለምን ልማት ይሠራል?” የሚል ሳይሆን፣ የጋራ ሀብቱና በጀቱ “ፍትሐዊ ተደራሽነት ሊኖረው ይገባል” የሚል መሠረታዊ መርህን የተከተለ ነው። ይሁን እንጂ የክልሉ ሕዝብ በተለያዩ ጊዜያት ያቀረባቸው በርካታ መሠረታዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር አቤቱታዎች፣ በተለይም በክልሉ አመራሮች ላይ ተገቢውን ምላሽ ሳያገኙ ለዓመታት ታፍነው ቆይተዋል።
ይባስ ብሎ በክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ የሚሰነዘሩት የተለያዩ ተጨባጭ የሙስና ክሶችና የአደባባይ ሌብነቶች በተለይም በከፍተኛ ሁኔታ መነጋገሪያ የሆነው የጎፋ የእርዳታ ገንዘብ ዝርፊያ እና የመንግሥት አመራሮች መዋቅራዊ ሙስና ታይቶ እንዳልታየ ተሸፍኗል።
በእነዚህ ተጨባጭ የሙስና ወንጀሎች ላይ የፌደራል መንግሥት እስካሁን ምንም ዓይነት ሕጋዊና የማስተካከያ እርምጃ አለመውሰዱ፣ በክልሉ ሕዝብ ዘንድ በመንግሥት ላይ ሙሉ በሙሉ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት እንዲነግሥ እያደረገ ይገኛል። ይህንን የሕዝብ ብሶትና የአመራሩን ብልሽት WT Media በተደጋጋሚ በሰነድና በማስረጃ አስደግፎ መዘገቡ የሚታወስ ነው።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 12 ዞኖችና 32 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች የጋራ ሰላማቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ ከተፈለገ፣ በሌብነትና በአድልዎ ላይ የተመሠረተው የአሁኑ የሀብት ክፍፍል በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል። የአንድን አካባቢ ልማት ከፍ በማድረግ ሌላውን ማግለልና “አንዱ ሲለማ ሌላው መሳቅ አለበት” በሚሉ ንግግሮች ማስተባበል ወይም የእርዳታ ገንዘብ ዝርፊያንና ሙስናን በዝምታ ማለፍ የሕዝብን ብሶት ከማባባስ ውጭ ፋይዳ የለውም፤ አካሄዱ በአከባቢው ከባድ መልካም አስተዳደር ችግር በመፍጠር በመንግሥት እና በህዝብ መካከል ጥራጥሬ የሚፈጥር መሆኑንም ምሁራን አክለው አስረድተዋል።