GridArt_20260713_172917068

ከ3.4 ቢሊዮን ብር በላይ መስተንግዶና ነዳጅ ላይ የባከነበት ዎላይታ ዞን የመንግስት ሠራተኛ ደመወዝ መክፈል ያቃተው ለምንድነው?

​በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኘው የዎላይታ ዞን ስር ባሉ 26 መዋቅሮች (ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች) የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የወሩ ደመወዝ በወቅቱ ባለመከፈሉ ምክንያት ለከፍተኛ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር መዳረጋቸውን ገልጸው አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ በምሬት እየጠየቁ ይገኛሉ።

ከተቀናጀው የWT Media የምርመራ ዘገባ እና የደረሰን ይፋዊ የኦዲት ሰነዶች መረዳት እንደሚቻለው ይህ የደመወዝ እጥረት የዞኑ የገንዘብ አቅም ማነስ ሳይሆን ሌብነት እና ምዝበራ መንግሥታዊ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያሳዩ በርካታ ተቋማዊ ብልሽቶች ውጤት መሆኑ ተረጋግጧል።

​የ WT Media ምርመራ ከተለያዩ የፍትሕ እና የኦዲት አካላት የደረሱትን ሰነዶች መነሻ በማድረግ ያጠናቀረው ሰፊ ትንተና እንደሚከተለው ቀርቧል።

​በፋይናንስ አዋጅና መመሪያ መሠረት የማንኛውም ዞን መደበኛ እና ካፒታል ሂሳቦች (የገቢ፣ ወጪ፣ ዝውውር፣ ተካፋይ እና ተሰብሳቢ) መንቀሳቀስ ያለባቸው በአንድ ዋና ማዕከላዊ አካውንት ብቻ መሆን ነበረበት።

ነገር ግን በዞኑ የፋይናንስ መዋቅር ውስጥ ሕግና መመሪያ የማይፈቅደውን ሌላ ትይዩ የባንክ አካውንት በመክፈት፣ የሕዝብን ገቢ የመሰወር እና የመቀራመት ሥራ በስፋት ተሰርቷል።

​ለዞኑ ፋይናንስ መመሪያ የተጻፈው ይፋዊ ደብዳቤ እንደሚያሳየው ከተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) እና ተመላሽ ሂሳቦች ጋር በተያያዘ የተሰበሰበ 30,000,000.00 (ሰላሳ ሚሊዮን ብር) በሕገወጥ መንገድ የተከፈተውን አካውንት ተጠቅሞ ለምዝበራ እንዲመች የባንክ ዝውውር መደረጉን ያረጋግጣል።
​
​የመንግሥት የፋይናንስ ቁጥጥር ሰንሰለትን ለመስበር በዞኑ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሐሰት ደረሰኞች መታተማቸውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ያካሄደው የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ያመለክታል።

​በክልሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በወጣው የኦዲት ግኝት መሠረት በዎላይታ ሶዶ ከተማ ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ስር ከ100 በላይ ሕገወጥ የደረሰኝ ካርኔቶች ታትመው ለአገልግሎት መዋላቸውና በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠር የመንግሥት ገቢ መመዝበሩ ተረጋግጧል።

​በተጨማሪም የኦዲት ሰነዱ እንደሚያሳየው በሆቴልና ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ግብር ከፋዮች የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ እና የግብር ክሊራንስ ቢሰጣቸውም የተሰበሰበው 21,296,650.72 ብር በባንክ ሂሳብ ማረጋገጫ (Statement) ላይ ሳይገባ መጥፏል። ግብሩ የሚሰበሰበው በፎርጅድ የባንክ አድቫይስ (Cash Deposit Advice) መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሶዶ ቅርንጫፍ ሰነዶች ያሳያሉ።


​
​የዎላይታ ዞን እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ የነበረበትን የባንክ ውዝፍ የማዳበሪያ ዕዳ ከንግድ ባንክ ሐዋሳ ቅርንጫፍ እና ከክልሉ ፋይናንስ ጋር በማወራረድ ሙሉ ክሊራንስ ወስዶ የነበረ ቢሆንም ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ አርሶ አደሩ እጅ በእጅ የገዛበትን ገንዘብ ለሚመለከተው አካል ሳያስተላልፉ አመራሮቹ ለግል ጥቅማቸው አውለውታል።

​ይህ በአርሶ አደሩ ስም የተሰበሰበ የባንክ ገንዘብ በግለሰቦች እጅ በመጥፋቱ ምክንያት ማዕከላዊው መንግሥት ዕዳውን ለማካካስ ከዞኑ ይላክ የነበረውን የበጀትና የደመወዝ ድልድል (የወጪ መረጃ) እንዲቆራረጥ አድርጓል። ይህ ቀጥተኛ ዝርፊያ ዞኑ በአሁኑ ወቅት የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንዲገጥመው ማድረጉን የምርመራው ውጤት ያሳያል።

​ማንኛውም የመንግሥት ግዥ በፋይናንስ መመሪያ የተደነገጉትን 6 ሕጋዊ የጨረታ መንገዶች መከተል ሲገባው በዎላይታ ዞን ግን ግዥዎች የሚፈጸሙት በከፍተኛ አስተባባሪዎች ቀጥተኛ ትዕዛዝ ብቻ ሆኗል።
​
በዎላይታ ሶዶ ዙሪያ ወረዳ በኩል በስህተት ተመዝግቧል በሚል 21,399,822.46 ብር ከመዋቅር ውጪ ለግለሰቦች ጥቅማጥቅም መከፋፈሉን የዞኑ የሥራ ልማት ጽሕፈት ቤት ደብዳቤዎች ያረጋግጣሉ።

​በተጨማሪም የ2018 የ’አይበክስ’ (IBEX) በጀት ሪፖርት እንደሚያሳየው ዞኑ 3.41 ቢሊዮን ብር ያህል ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ያደረገው እንደ መስተንግዶ (6233)፣ ነዳጅ (6217)፣ ለድርጅቶች ስጦታ (6412)፣ ለጉልበት ክፍያ (6255) እና ውሎ አበል (6231) ባሉ የብክነት መደቦች ላይ ብቻ ነው።

​የዞኑ አስተዳደር ከዎላይታ ሶዶ ከተማ የተሰበሰበውን ገቢ ሳይጨምር በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመቱ 5.3 ቢሊዮን ብር ሰብስቤያለሁ በማለት ይፋዊ ሪፖርት ቢያቀርብም የ26ቱ መዋቅር አጠቃላይ የሠራተኞች ዓመታዊ ደመወዝ ግን 3.71 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው። ዞኑ ከሰበሰበው ገቢ በተጨማሪ ከክልሉ ፋይናንስ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ የተላከለት ሲሆን በአጠቃላይ 12.83 ቢሊዮን ብር ገቢ ሊኖረው ይገባ ነበር።

​ይህ ሁሉ ጥሬ ገንዘብ እያለ ዞኑ የወሩን ደመወዝ በወቅቱ መክፈል አለመቻሉ እና የወረዳ ሠራተኞች የሠሩበትን የውሎ አበል (አበል) ሙሉ በሙሉ መከልከላቸው፣ የቀረበው የገቢ ሪፖርት በባንክ ስቴትመንት ያልተረጋገጠ “የውሸት ሰነድ” መሆኑን ከጥርጣሬ በላይ ያረጋግጣል።
​
​በዎላይታ ዞን ማዕከል የተዘረጋው ይኸው የበጀት ምዝበራ ወደ ታችኛው መዋቅር ሲወርድ ደግሞ ከመሬት ወረራ፣ ከጥብቅ ደኖች ሽያጭ፣ ከሴፍትኔት እና ከቃልም እርዳታ እህል ዝርፊያ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ቀደም ሲል የWT Media ምርመራ ዘገባ ማጋለጣቸው ይታወሳል።

​የመንግሥት ሠራተኞች “በብሉሹ አመራር ምክንያት ለተራብንበት እንግልት አስቸኳይ መፍትሔ ይሰጠን” እያሉ ባሉበት በአሁኑ ወቅት የፌደራል እና የክልሉ የፍትሕ አካላት በሰነድ የተደገፉትን እነዚህን ግልጽ የሌብነት ወንጀሎች መሠረት በማድረግ በአመራሩ ላይ የማያዳግም የሕግ እርምጃ እንዲወስዱ ማኅበረሰቡ በጥብቅ እየጠየቀ ይገኛል።

WT Media በሰነድ የተደገፉትን እነዚህን ከባድ የፋይናንስ ብክነቶች፣ የደመወዝ መዘግየት ምክንያቶች እና የተቋማዊ አሠራር ጥሰቶችን በተመለከተ የሙያዊ ሚዛናዊነት መርህን በመከተል ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የዎላይታ ዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ከፋይናንስ መመሪያው ማብራሪያና ምላሽ ለመጠየቅ ተደጋጋሚ ጥረት አድርጓል።

​ይሁን እንጂ የሚመለከታቸው የዞኑ አካላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን ጉዳዩን በዝምታ ማለፍን መርጠዋል። ይህ የአመራሩ ምላሽ የመንፈግ አካሄድ በሠራተኛው እና በሕዝቡ ዘንድ ያለውን የአስተዳደር ግልጽነት ጥያቄ ይበልጥ የሚያጠለሽ ሆኗል።