GridArt_20260728_184948186

​የዎላይታ ሶዶ ከተማ የታሪክ፣ የባህል፣ የንግድና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና ማዕከል መሆኗ ቢታወቅም በአሁኑ ወቅት በከተማዋ እየታዩ ያሉ የልማት ሥራዎች መስተጓጎልና መዘግየት የከተማዋን ነዋሪዎች በእጅጉ እያሳሰበ ይገኛል።

ከተማዋ ወደፊት መራመድ ሲገባት በተጀመሩና በተንቀራፈፉ ፕሮጀክቶች ምክንያት ወደ ኋላ እየተሳበች ትገኛለች የሚሉ ቅሬታዎች ይሰማሉ።

​ከተማውን ከተደቀነባት የልማት ማነቆ ለማውጣት አስቸኳይ ምላሽ የሚያሻቸው ሦስት አንገብጋቢ ጉዳዮች በነዋሪዎች ዘንድ ተነስተዋል።

​ለከተማዋ ብቻ ሳይሆን ለመላው የአካባቢው ሕዝብ ዋነኛ የጤና ጋሻ በመሆን ከ1920 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ የነበረው ትልቁ የመንግሥት ሆስፒታል በድንገተኛ እሳት አደጋ ጉዳት ከደረሰበት ቆይቷል።

በወቅቱ በፍጥነት ይጠገናል ተብሎ ቃል ቢገባም በተግባር ግን ዛሬም ድረስ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት በሚያስችል ደረጃ አልተገነባም።

​ይህ መዘግየት በተለይም የጤና መድህን ተጠቃሚ በሆኑ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ እያስከተለ ይገኛል።

የሆስፒታሉ መልሶ አለመገንባትና የአገልግሎት መቋረጥ አቅመ-ደካሞችና አርሶ አደሮች ተገቢውን ሕክምና በሰዓቱ እንዳያገኙ በማድረጉ ሳነሳ ለከፍተኛ የሞት አደጋ እየተጋለጡ ይገኛሉ። ሆስፒታሉ በአስቸኳይ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት እንዲደረግ ነዋሪዎች ለ WT Media በሰጡት አስተያየት ላይ ጠይቀዋል።

​የከተማውን የትራፊክ ፍሰት ከማሳለጥም ባሻገር ለከተማው የውበት መገለጫ መሆን የሚገባው ከሌዊ ሪዞርት እስከ ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ያለው ዋነኛ የከተማ ውስጥ መንገድ ከተጀመረ ረጅም ጊዜ ተቆጥሯል።

ፕሮጀክቱ በተንቀራፈፈ ጉዞው ምክንያት የንግድ እንቅስቃሴን ከማስተጓጎሉም በላይ በነዋሪው፣ በተማሪውና በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ እንግልት እየፈጠረ ይገኛል።

ለአመታት ተጓትቶ እስካሁን ባለማለቁ በኅብረተሰቡ ዘንድ ዘርፈ-ብዙ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች እየደረሱ ይገኛሉ።
​
ከተማን ማዘመንና የኮሪደር ልማትን መሥራት መልካም ቢሆንም በየአቅጣጫው መንገዶችን ቆፍሮና አፍርሶ ያለ አንዳች መፍትሔ ማስቀመጥ ከተማዋን ወደ ፍርስራሽና አቧራ ቀጠና እየቀየራት ይገኛል።

የተቆፈሩት መንገዶች በአስቸኳይ ተሠርተው ካላለቁ በቀር ልማቱ የነዋሪውን የዕለት ተዕለት ሕይወት የማስተጓጎል ሰበብ እየሆነ መምጣቱ ይነገራል።

​የዎላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች የገባችበትን የልማት መቀዛቀዝ ቆም ብሎ በመፈተሽ እነዚህን የቆዩ ፕሮጀክቶች በአስቸኳይ ወደ ማጠናቀቂያው እንዲደርሱ የሚመለከታቸው አካላት ጥብቅ ምላሽ እንዲሰጡ ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።