ከዓመት በፊት በእሳት አደጋ የወደመውና ከሦስት ሺህ በላይ አቅመ-ደካሞችና አርሶ አደሮች ለከፍተኛ የጤና እክልና ሕልፈተ ሕይወት መዳረጉ የሚነገርለት የታሪካዊው የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል (ኦቶና ሆስፒታል) ዳግም ግንባታ ውል ዛሬ ሐምሌ 23 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ መፈረሙ ተገልጿል።

ከአንድ ወር በፊት WT Media ከባለሥልጣናት ባገኘው መረጃ የሆስፒታሉ ዳግም ግንባታ እንቅስቃሴ እንደሚጀመር ማጋራቱ ይታወሳል። ዛሬ ላይ ግንባታው መጀመሩ አዎንታዊ እርምጃ ቢሆንም የኅብረተሰቡ ድምጾች እንደሚያሳዩት ጅምሩ ብቻውን በቂ አይደለም። እንደ ከተማው አስፋልት መንገዶች እና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች ለዓመታት ተጀምረው በመጓተታቸው ከፍተኛ እንግልት እንደፈጠሩ ሁሉ የኦቶና ሆስፒታልም “ተጀመረ” በሚል ብቻ ለአመራሮች የጉብኝት ማዕከል ሆኖ እንዳይቀረድ ሥጋት አለ።
የዎላይታ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽንና ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ከዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስና ሕክምና ኮሌጅ ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል (ኦቶና ሆስፒታል) ጋር ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በሚወጣ በጀት ፕሮጀክቱን ለማከናወን ውል ተፈራርመዋል።
የዎላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በበኩላቸው በእሳት አደጋ የተስተጓጎለው የሆስፒታሉ አገልግሎት በፍጥነት እንዲመለስ ፕሮጀክቱ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኮንስትራክሽን ድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሀብታሙ ፋንታ በይፋዊ ማህበራዊ ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት፤ «ኦቶና ሆስፒታል ታርካዊነቱን ጠብቀን ጥራቱን አሻሽለን ለህዝባችን በአጭር ግዜ አጠናቀን ዳግም ብሥራተ እናደርጋለን።» በማለት የቁርጠኝነት መግለጫ አጋርተዋል።

ለአካባቢው ማኅበረሰብ በተለይም የጤና መድህን ተጠቃሚ ለሆኑ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው ፈጣን መፍትሔ እንዲሰጥ የሚከተሉት ዋና ዋና ጥያቄዎች ተነስተዋል፦
ግንባታው መጀመሩ ቢነገርም ሕዝቡ ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት ማግኘት የሚጀምረው መቼ እንደሆነ የሚገልጽ ግልጽ የጊዜ ገደብ አልተቀመጠም። ውሉ መፈረሙ ቢነገርም ፕሮጀክቱ በመሬት ላይ ተጠናቆ ሕዝቡ አገልግሎት ማግኘት የሚጀምረው መቼ እንደሆነ የሚገልጽ ግልጽ የመጠናቀቂያ ጊዜ ገደብ በግልጽ ባለመነገሩ በነዋሪዎች ዘንድ ሥጋት ፈጥሯል።
ለዚህ የጤና ተቋም መልሶ ግንባታ የተመደበው ትክክለኛ የበጀት መጠን (ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ቢገለጽም) ይፋዊና ዝርዝር መሆን ይገባል።
እንደ ከተማው አስፋልት መንገዶች እና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች ለዓመታት ተጀምረው በመጓተታቸው ከፍተኛ እንግልት እንደፈጠሩ ሁሉ ፕሮጀክቱ ከባዶ ቃልና ከወሬ ባለፈ በተቀመጠለት ፍጥነትና ጥራት እንዲጠናቀቅ ጥብቅ ክትትልና ግልጽነት እንዲኖር ነዋሪዎች እና አስተያየት ሰጪዎች በጥብቅ እየጠየቁ ይገኛሉ።
በዚህ ዙሪያ WT Media ከዚህ በፊት ባደረጋቸው ጥልቅ ዘገባዎች የሚከተሉትን ዋና ዋና ጉዳዮች ማስታወሱ ይታወሳል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ጥላሁን ከበደ “እናክመው” በሚል መሪ ቃል የሆስፒታሉን መልሶ ግንባታ ለማከናወን ይፋዊ ጥሪ ካስተላለፉ ጀምሮ፣ የክልሉና የዞኑ ባለሥልጣናት ግንባታው የሚጀመርበትን ተጨባጭ ቀን ከመናገር ይልቅ በባዶ ተስፋ ቃላት ለአንድ ዓመት ሲያራዝሙት ቆይተዋል።
ሆስፒታሉ አገልግሎት ማቋረጡንና የጤና መድህን ተጠቃሚ የሆኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችና አቅመ-ደካሞች ወደ ግል ሕክምና ተቋማት ሄደው መታከም ባለመቻላቸው በየቤቱና በየቀበሌው የሚሞቱ ዜጎች ቁጥር ከ3 ሺህ በላይ እንደሚገመት WT Media በዘገባዎቹ አጋልጧል።
ለሆስፒታሉ መልሶ ግንባታ ከተለያዩ ዜጎችና ድርጅቶች የተሰበሰበው የገንዘብ መጠንና ቁሳቁስ የት እንደደረሰ ግልጽ ባለመደረጉ እና ኦዲት ተደርጎ ለሕዝብ ይፋ ባለመሆኑ ከፍተኛ የሕብረተሰብ ቅሬታ መፈጠሩ ተመልክቷል።
ሆስፒታሉ ከመውደሙ ባሻገር ከ100 ዓመታት በላይ ሲያገለግል የቆየው የጤና ሳይንስና ሕክምና ኮሌጅ ከልህቀት ማዕከልነት እንዲወጣና እንዲዘጋ የሚደረግ ድብቅ ፖለቲካዊ ሴራ መኖሩን እና የጤና ቱሪዝም ፍሰትን ወደ ሌላ አካባቢ ለማዞር ታቅዶ እንደሚሰራ ሚዲያው አጋልጦ ነበር።
የኦቶና ሆስፒታል ዳግም ግንባታ በውል መፈረሙና ሥራ መጀመሩ የሚበረታታ አዎንታዊ ጅምር ቢሆንም፤ ማኅበረሰቡ ከዚህ ቀደም የነበሩ የተጓተቱ የመሠረተ ልማት ቃልኪዳኖችን በመጥቀስ ጥርጣሬውን ገልጿል።

በመሆኑም የተሰጠው የበጀት መጠን እና የኮንስትራክሽን ተቋሙ የገባው የቁርጠኝነት ቃል ባዶ ቃል ሆኖ ሳይቀር፣ ሕዝቡ ከእንግልት ተላቆ በፍጥነት የጤና አገልግሎት ማግኘት እንዲችል ጥብቅና ግልጽ የሆነ የክትትል ሥራ የሚጠይቅ ወቅታዊ ጉዳይ ሆኗል።