GridArt_20260807_162700361


በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዎላይታ ዞን እና በጋሞ ቁጫ መካከል እየተካሄደ የነበረው የደሜ ድልድይ እና የመንገድ ግንባታ በድጋሚ እንዲቋረጥ መደረጉ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣና ቅሬታ መቀስቀሱ ተገልጿል።

​የክልሉ ገጠር መንገድ ባለሥልጣን ፕሮግራም አካል የሆነው ይህ ግንባታ፤ በዎላይታ ዞን በኩል የኪንዶ ዲዳዬ እና የካዎ ኮይሻ ወረዳ ሕዝብን ከጋሞ ዞን ቁጫ አልፋ ወረዳ ሕዝብ ጋር የሚያገናኝ ነው። በተለይም በታሪኩ ለሕዝብ ከሚሰጠው ጥቅም ይልቅ በጉዳቱ የሚታወቀውና በየዓመቱ በቁጥር መገመት የማይቻል የሰው ሕይወትና የቤት እንስሳትን ሲያሰምጥ የነበረው በደሜ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው ድልድይ ሥራ «በከፍተኛ አመራር ትዕዛዝ» ባልታወቀ ሁኔታ መቆሙን በግንባታው የተሳተፉ አካላት ለ WT Media አረጋግጠዋል።

የዚህ መንገድና ድልድይ ግንባታ አጀማመሩና ዋና ዓላማው ሁለቱ የዎላይታ እና የቁጫ ወንድማማቾች ሕዝቦች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች እንዲሳሰሩ፣ በደስታም ሆነ በሐዘን አብረው እንዲኖሩ እና በውሃ ሙላት ምክንያት የሚደርሰውን የሰው ሕይወት መጥፋትን ለማስቀረት ታስቦ የነበረ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጸሉ።

​በሌላ በኩል ይህ አከባቢ «የጥቁር ወርቅ» በመባል የሚታወቀውን የዚሁ አካባቢ አንጡራ ሀብት የሆነውን በርካታ የድንጋይ ከሰል ክምችት እና ሌሎች ማዕድናት የያዘ መሆኑ ይታወቃል። ስለዚህም መንገዱ ለህዝብ አገልግሎት ከመሰጠቱ ባለፈ ለመንግሥት ከፍተኛ ገቢ ለማስገኘት እና ለሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የጎላ ሚና እንደሚኖረው ታሳቢ ተደርጎ ነበር።
​
ቀደም ሲልም በጋሞ ዞን በኩል በደረሰ ከፍተኛ ጫና እና በተቀነባበረ ሴራ ግንባታው እንዲቆም መደረጉን WT Media ከ8 ወር በፊት ይታወሳል። በወቅቱ በግንባታው ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሠራተኞች ከጋሞ ዞን በኩል በደረሰባቸው ማስፈራሪያና ጫና ሥራቸውን ለማቆም ተገደዋል።

እንዲያውም ግንባታውን ለማስቆም በታቀደ ሴራ በድንጋይ ላይ «አንድም ሰው በዚህ አካባቢ እንዳይንቀሳቀስ» የሚል ትዕዛዝ በታፔላ ተጽፎ መለጠፉ በሠራተኞቹ ላይ ከፍተኛ የደኅንነት ስጋት መፍጠሩ ተገልጿል።

​ጨረታውን አሸንፎ ወደ ሥራ የገባው Prop Construction PLC የተባለ ተቋራጭ በዎላይታ በኩል ያለውን የቁፋሮ ሥራ አጠናቆ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ለመሸጋገር ሲሞክር በጋሞ ዞን በኩል በታጣቂዎችና በከፍተኛ አመራሮች ትዕዛዝ ጫናዎች ሲፈጠሩበት ቆይቷል።

ዓላማውም ተቋራጩ ተስፋ ቆርጦና ቅድመ ክፍያውን ሳይወስድ ሥራውን ጥሎ እንዲወጣ ለማድረግ የሚደረግ ስልታዊ ጫና መሆኑን ምንጮች አመላክተዋል፤ በዚህም ሠራተኞች ለደኅንነታቸው በመስጋት ሥራ ለቀው መውታታቸው ተሰምቷል።
​
በወቅቱ የዎላይታ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል አይሳሮ እና የኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ዋኬ ግንባታው መጀመሩን እንደ ታሪካዊ ስኬት ቢገልጹትም በመሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ከዚህ በተቃራኒ ሆኖ የክልሉ መንግሥት “ከምርጫው ማግሥት ጠንካራ መንግሥት” በሚል መሪ ቃል የገባቸውን የልማት ኪዳኖች በተግባር ማሳየት እንዳልቻለ አሳይቷል።

​ለበርካታ ዓመታት ታቅዶና ተጀምሮ ሳይሳካ የዘለቀውን ከ15 በላይ ቀበሌያትን የሚያገናኘውን ይህን ወሳኝ ፕሮጀክት አሁንም በፖለቲካዊ ሴራ ማደናቀፍ “ለዎላይታና ለቁጫ ሕዝብ ያለውን ጥላቻና ንቀት በገሃድ ማሳየት ነው” ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች በብርቱ አውግዘዋል።

​የአካባቢው ነዋሪዎች ይህንን በግፍ የሚፈጸም የልማት ማደናቀፍ ተግባር የፌዴራል መንግሥትና የበላይ አካላት በቅርበት እንዲመለከቱትና ጣልቃ ገብተው እንዲያስቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

WT Media በጉዳዩ ዙሪያ ከጋሞ ዞንና ከክልሉ መንግሥት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት እስካሁን ባይሳካም፣ የግንባታውን ሂደትና የሚፈጸሙ ማናቸውንም ሕገ-ወጥ መሰናክሎች በቅርበት መከታተሉን ይቀጥላል።

​🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን 🙏

​Voice of Marginalized Community – WT Media