የደቡብ ኢትዮጵያ ወጣቶች የግዳጅ ውትድርና እና ሶስቱ ብሔሮች በየጊዜው የሚፈጥሩት የፖለቲካ ቀውስ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱ ከፍተኛ ቅሬታ እየፈጠረ ስለመሆኑ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ሁለገብ ቀውሶች፣ የግዳጅ ወታደር ምልመላ አፈሳዎች እንዲሁም የሀገሪቱን ፖለቲካ የተቆጣጠሩት የሶስቱ ብሔር ሊቃኖች ፍላጎት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ምሁራንና ከየአቅጣጫው የደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በሻሸመኔ፣ በሀዋሳ፣ በዝዋይ፣ በአዲስ አበባ፣ መቂ እና በሌሎች ከተሞች ቀን ሰራተኛ፣ ጉልበት ሰራተኛ እና ልስትሮ በመሆን ሕይወታቸውን ለመምራት የተሰማሩ ከደቡብ ኢትዮጵያ በተለይም በብዛት የዎላይታ ወጣቶች ለሰራዊትነት በኃይል እየታፈሱ መሆኑን ለ WT Media የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
በዎላይታ ዞን የተለያዩ አካባቢዎችም የተሰጠውን ኮታ ለመሙላት ሞተረኞች እና ተማሪዎችን ጨምሮ ወጣቶች መንገድ ላይ ሲገኙ በግድ ወደ ውትድርና እንዲገቡ እየተደረገ ይገኛል።
ለኦሮሚያ፣ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ሲዳማ እና ሌሎች ክልሎች የተሰጠውን የውትድርና ኮታ ለመሙላት በክልሉ የስራ ዕድል ባለመኖሩ ምክንያት ለስራ ወደ ሌሎች ከተሞች የሄዱ ወጣቶችን በግድ መውሰድ መባባሱን WT Media ከየአካባቢው ለማረጋገጥ ችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰሜኑ ጦርነትና ግጭቶች ያስከተሉት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከባድ መሆኑ ይነገራል።
“ኢትዮጵያ ማለት የ3ቱ (የአማራ፣ የትግራይና የኦሮሞ) ሀገር ነች፤ የደቡብ ልጅ የትኛው ዳር ድንበር ላይ ነው የሚዋጋው? ሦስቱ በፈጠሩት ምስቅልቅል የደሃ ልጅ ለምን ይረግፋል?” የሚል ጠንካራ ተቃውሞ በአካባቢው እየተሰማ ይገኛል።
ከአድዋ ጀምሮ የኢትዮጵያ ህልውና እንዲጠበቅ የሰሜኑ ፖለቲከኞች በሚፈጥሩት ችግር ግንባር ቀደም ዋጋ የሚከፍለው አብዛኛው የደቡብ ህዝብ መሆኑ በከባድ ቅሬታነት መልካም አስተዳደር እጦት ሆኖ እየተነሳ ነው።
በአማራና በትግራይ ክልል በተከሰተ ጦርነት ሚሊዮኖች ከትምህርት ውጭ መሆናቸውን፣ እናቶች በዛፍ ስር መገላገላቸውን እና መሰረተ ልማቶች መውደማቸውን ያነሱት አስተያየት ሰጪዎች ከደቡብ ኢትዮጵያ በመከላከያ ተሰልፈው የሞቱት ዜጎች ቁጥር እንኳን እንደማይታወቅ ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሶስቱ ብሔሮች (አማራ፣ ኦሮሞ እና ትግራይ) ሊቃኖች ብቻ መዘወሩ ትልቅ አገራዊ ቀውስ መሆኑን በጉዳዩ ዙሪያ ለ WT Media የሚያነሱት ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ይህ አካሄድ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን እንደሚጎዳ ይገልጻሉ።
የሀገረ መንግሥት እና የብሔረ መንግሥት ግንባታው አንካሳ መሆን እንዲሁም ፖለቲካው ሁሉንም ዜጋ የሀገር ባለቤት በሚያደርግ መልኩ ባለመዘመኑ የተረጋጋች ሀገር መፍጠር አልተቻለምም ይላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን ጨምሮ የፖለቲካ አካላት እና አንጋፋ ፖለቲከኞች (ለምሳሌ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና) የሀገሪቱን ልዩነቶች ከሶስቱ ብሔር ማዕቀፍ ውጭ ማየት እንዳቃታቸው ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ያነሳሉ።
ሱማሌን ጨምሮ 80ዎቹን ብሔሮች መርሳት እና ሀገሪቱን እንደ ሶስቱ ብሔሮች የግል ንብረት አድርጎ መመልከት መፍትሔ እንደማያመጣ የገለጹት ምሁሩ፤ መፍትሔው ከሶስቱ ብሔሮች ውጭ ያሉ ሊቃኖችና ሕዳጣን ለባለቤንታቸው መታገል እና የፈላጭ ቆራጭነት አባዜን በአንድነት መቃወም እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ምሁራን በአጠቃላይ በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ “የሶስቱ ብሔር ሊቃኖች ፍላጎት ብቻ የሰፈነበትና ሌሎችን 80ዎች ያገለለ አዙሪት መፈጠሩ አገራዊ ህልውናን ለከፍተኛ አደጋ ዳርጎታል” ይላሉ።
“ከሰሜኑ ግጭት መዘዝ አንስቶ እስከ ደቡብ ወጣቶች የግዳጅ አፈሳ ድረስ ያለው ሰቆቃ፤ የሕዝብን መብትና ደህንነት የሚፈታተን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ይህ በደቡብ ወጣቶች ላይ እየተፈጸመ ያለው ስልታዊ የጉልበት እና የውትድርና ማፈስ ዘመቻ ከኢኮኖሚያዊ ስብራት ባለፈ ከባድ ማህበራዊ ቀውስ እየፈጠረ ይገኛል። ሕዝቡ ምክንያታዊነት በሌለው ፖለቲካ ከዕለት ኑሮው እስከ ህልውናው ድረስ እንዲሰቃይ መደረጉ ሊቆም የሚገባው ትልቅ አገራዊ ግፍ ነው” በሚል ይገልፃሉ።
ስለሆነም ጦርነትን በማስወገድ ፍትህና እኩልነት የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት ከሶስቱ ብሔር የሞግዚትነት አስተሳሰብ ወጥቶ የሁሉንም ዜጎች ድምፅ ማክበር እና የኃይል እርምጃዎችን በአስቸኳይ ማስቆም ወሳኝ መፍትሔ ነው” በሚል አክለዋል።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media