ScreenShot_9_1_2026_3_46_01_PM

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር እየተካሄደ ያለው የቤቶች ማፍረስ እና የከተማ እድሳት ዘመቻ ህጋዊ የቤት ባለቤቶችንና ነዋሪዎችን ለከፍተኛ እንግልትና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እየዳረገ መሆኑ ተሰምቷል።

በከተማዋ ከረጅም ዘመናት አንስቶ በባለቤትነት ይዘውት በነበሩት መኖሪያ ቤቶች ላይ ያለ ምንም በቂ ማስተካከያ እና ፍትሃዊ ምላሽ እጅግ አሳሳቢ የውድመት እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ።

በጉዳዩ ላይ ቅሬታቸውን የሚያሰሙ ነዋሪዎች እንደገለጹት ቤቶቻቸው ትክክለኛ የባለቤትነት ካርታ እና ህጋዊ ሰነዶች ያሏቸው መሆናቸውን አረጋግጠዋል። 

ይሁን እንጂ የከተማው አስተዳደር ባለስልጣናት ህጋዊ ሰነዶቹን እና ማስተባበያዎችን ወደ ጎን በመተው፣ ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያና የካሳ ስምምነት ቡልዶዘሮችን በመጠቀም ቤቶችን እያወደሙ ይገኛሉ።

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት እርምጃው በዜጎች መሰረታዊ መብቶች ላይ ያነጣጠረ እና ከህግ አግባብ ውጭ የሚከናወን ግፍ ነው። ህጋዊ የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ እያላቸው በተፈጸመው በዚህ ኢ-ሰብአዊ ተግባር ሳቢያ በርካታ ቤተሰቦች ከለላ አልባ ሆጸው ለከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ ተጋልጠዋል።

WT Media ጉዳዩን አስመልክቶ ምላሽ ለማግኘት እና የከተማ አስተዳደሩን አቋም ለማካተት ለተመለከተው አካልና ለኃላፊዎች ጥረት ቢያደርግም እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ ሊሰጥ አልቻለም። የሚመለከታቸው አካላት ለቀረበው ጥያቄ አጸፋ ባለመሰጠታቸው የነዋሪዎቹ ቅሬታና ስጋት ከፍ እንዲል አድርጓል። 

የዜጎችን ሰብዓዊና ንብረታዊ መብቶች የሚጥሰው ይህ አሰራር በአፋጣኝ እንዲቆም የሚጠይቁት ነዋሪዎች ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል እና ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በማድረስ ፍትህ እንዲሰፍን ድምፃቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media